ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል

ኢትዮጵያን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመወከል በ46 ቡድኖች መካከል ሲካሄድ በነበረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ቡናማዎቹ የጦና ንቦቹን 2ለ1 በማሸነፍ ቻምፒዮን ሆነዋል።

9 ሰዓት ሲል የአዲስ አበባ ስታዲየም መያዝ ከሚችለው ቁጥር በላይ እጅግ በርካታ በሆኑ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ታጅቦ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ምክንያት ቀዝቃዛ ነበር። ሆኖም 5ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች ግብ አስቆጥረው የተሻረበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር።


ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ በኩል መጠነኛ ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል ዮሐንስ እና በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ በአማኑኤል አድማሱ አማካኝነት ሙከራዎችን አድርገው የመጀመሪያው ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ሁለተኛውን ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ይዞታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሳያስመለክተን በቀጠለው ጨዋታ በቡናማዎቹ በኩል አሥራት ቱንጆ እና ሬድዋን ናስር ካደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ግልጽ የማግባት ዕድል ሳይፈጠር አጋማሹ ያለ ጎል ተጠናቋል።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል ግሩም አጀማመር ያደረጉት የጦና ንቦቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በቀኝ መስመር የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ቢኒያም ፍቅሩ በተረከዙ በመምታት ለአበባየሁ ሀጂሶ አቃብሎት አበባየሁም ኳሱን በድንቅ አጨራረስ ግብ ጠባቂው ባጠበበበት በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ በተረጋጋ ሁኔታ ሲታትሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አማኑኤል ዮሐንስ ሳጥን ውስጥ በአበባየሁ ሀጂሶ ጥፋት ተሠርቶበታል በሚል በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ውሳኔ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ዋሳዋ ጄኦፍሪ በግብ ጠባቂው የቀኝ እጅ በኩል የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ለመያዝ ጥረት ቢያደርግም ኳሱ እጁን ጥሶት ግብ ሆኗል።


ኳሱን ከመሃል ሜዳ በጀመሩ በሴኮንዶች ልዩነት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች 68ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ብሥራት በቀለ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አበባየሁ ሀጂሶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ 1-1 ተጠናቋል።

በጭማሪው 30 ደቂቃ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ ዘለግ ያለውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በዲቻ የግብ ክልል ማሳለፍ ይዘዋል። በተለይ በ97ኛው ደቂቃ አማኑኤል አድማሱ ከግራ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ መስፍን ታፈሰ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታል። ከደቂቃዎች በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ዲቻዎች በተጠቁበት መስመር በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ጥረው ተመልሰዋል።


በ113ኛው ደቂቃ ከመዓዘን የተሻማ ኳስ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል በእጅ ተነክቷል በሚል ቡናማዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ዋሳዋ ጄኦፍሪ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። በቀሩት ደቂቃዎች በከፍተኛ ውጥረት የቀጠለው ጨዋታው ድቻዎች ከዳኝነት ቅራኔ ጋር ጨዋታውን እየከወኑ ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ስንታየሁ ወለጬን ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት በቀይ ካርድ ያጡት ቡናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት ሁለት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።