የኢትዮጵያ የሴቶች አሰልጣኞች የሙያ ማህበር ከተመሰረተ የአንድ ዓመት እድሜ ሲኖረው ይህንን በማስመልከት ጊዜያዊ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴን በአዲስ የመተካት እንዲሁም በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤውን ለየት ባለ መልኩ በተለያየ ፕሮግራሞች አከናውኗል።
በአዳማ ካኖኦፒ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተደረገው የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ የአሰልጣኞች የሙያ ማህበር የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የመክፈቻ ንግግር ከተከፈተ በኋላ የጉባኤው አጀንዳዎች በአሰልጣኝ ብዙእየሁ ዋዳ ቀርቦ ከፀደቀ በኃላ የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት በሆኑት አሰልጣኝና ኢንስትራክተር መሰረት ማኔ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ የተሰሩ ሥራዎችን አብራርተዋል።
በማስከተልም የማህበሩ የሂሳብ ሹም በሆኑት አሰልጣኝ ዩሴፍ ገ/ወልድ የፋይናንስ ሪፖርት አቅርበዋል። አሰልጣኝ ዩሴፍ ገ/ወልድ በገለፃቸው የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር በበጀት ዓመቱ 132 ሺ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ገቢ አድርጎ 52 ሺ ወጪ መደረጉን ይፋ በማድረግ የተለያዩ የውጪ ኦዲት ሪፖርትም አቅርበዋል።
በመቀጠልም ማህበሩ በግሩም አቀራረብ የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ በሚል ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን እስካለበት ድረስ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር አባሎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚወዳደሩ የየክለቦች አንበሎች እንዲሁም ረዥም ጊዜ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እስካሁን ደረስ በመጫወት ላይ የሚገኘ ተጫዋቾች በተገኙበት ዶክመንተሪ በአሰልጣኝ እና ኢንስትራክተር መሰረት ማኔ አማካኝነት መቅረብ ችሏል።
በመቀጠልም በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ላይ እስካሁን ደረስ ለረዥም አመት መጫወት የቻሉ ተጫዋቾች :-
1.ሕይወት ረጉ (መቻል)
2.ወይንሸት ፀጋዬ (ባህርዳር ከነማ)
3.ብርቱካን ገ/ክርስቶስ (ንግድ ባንክ)
4.ሽታዬ ሲሳይ (ኤሌክትሪክ )
5.ማርታ በቀለ (ኤሌክትሪክ )
6.ብዙሀን እንዳለ (ሀዋሳ ከተማ)
7.ሩታ ያደታ (አዲስ አበባ ከተማ)
8.ሒሩት ደሴ (ሲዳማ ቡና)የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ የሙያ ማህበሩ ላበረከቱት የረዥም ጊዜ ግልጋሎት የምስክር ወረቀት እና የእውቅና ሽልማት አብርክቷል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር እንዲቋቋም በሙያ እና በእውቀት ድጋፍ ላደረጉ አቶ ያዛቸው አበበ እንዲሁም አቶ ኤርሚያስ የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ሽልማት አበርክቷል። አያይዞም የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር የአንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት ፣ ለካኖኦፕ ሆቴል እና ለትዕንግርት ስፖርት ሚዲያ የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ሽልማት አበርክተዋል።
በመቀጠልም ማህበሩ አንደኛ አመቱን በማስመልከት የየክለብ አንበሎች እና ሴት አሰልጣኞች በጋራ በመሆን የተዘጋጀውን የአንደኛ ዓመት የሚዘክር ኬክ መቁረስ ችለዋል።
በመጨረሻም በጊዜያዊነት ለአንድ አመት የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማህበር ሲመሩ የቁዩት የስራ አስፈጻሚ በማሰናበት አዲስ ምርጫ በአስመራጭ ኮሚቴ በማከናወን የድምፅ መስጠት ስነስርዓት በማከናወን አስመራጭ ኮሚቴው እንደሚከተለው ውጤቱን ማሳወቅ ችሏል :-
መሰረት ማኔ 23 ድምፅ
ብርሃኑ ግዛው 21 ድምፅ
ፍሬህይወት አሳዬ 20 ድምፅ
ብዙየሁ ዋዳ 16 ድምፅ
ኩመራ በቀለ 16 ድምፅ በማግኘት እና በህግ እና ደንቡ መሰረት የተመረጡት ስራ አስፈጻሚዎች ባሳወቁት የስራ እና የስልጣን ክፍፍል መሰረት :-
1.የማህበሩ ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ግዛው
2.የማህበሩ ም/ፕሬዚዳንት መሰረት ማኔ
3.ጸሐፊ ኩመራ በቀለ
4.ገንዘብ ያዥ ፍሬህይወት አሳዬ
5.ሒሳብ ሹም ብዙየሁ ዋዳ በመሆን የተሹሙ ሲሆን በመቀጠልም ስራ አስፈጻሚዎች በስራቸው የተለያዩ ንዑሳአን ኮሚቴ በማቋቋም እና የስራ ድርሻ በመስጠት እና በምርጫው የማህበሩ ፕሬዚዳንት በመሆን በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት አዲሱ ፕሬዚዳንት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለጉባኤው አባላት የሴቶች እግር ኳስ እንዲያድግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሥራዎችን እንዲሰሩ አደራ ብለው የመዝጊያ ንግግራቸውን አድርገው የጠቅላላ ጉባኤ ተገባዷል።
* መረጃውን ከማኅበሩ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዳዊት አግኝተናል።