[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
13ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ በክለቦች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 የክለቦች የፋይናንስ ሥርዓት ላይ አዳዲስ ደንቦች መፍትሔ ያመጡ ይሆን ?
በሀገራችን እግርኳስ የክለቦችን ወጪ ገቢ መመርመር ሳያስፈልግ በእርግጠኝነት ወጪ፣ ወጪ እንደገና ወጪ የሚሉ ልውውጦችን በሂሳብ መዝግባቸው ላይ የመመልከታችን ነገር የሚያጠያይቅ አይደለም። ከዚህ ጋር ተነፃፃሪ የሆነ እግርኳሳዊ ገቢ በሌለበት ሁኔታ ይህ ሂደት ምን ያህል በቀጣይነት ያስጉዛቸዋል የሚለው ጉዳይ ለዘመናት ምላሽ ሳያገኝ ለዛሬ አድርሶናል።
አሁን ላይ ከሊጉ የስያሜ መብት ሽያጭ እና ከቴሌቪዥን መብት ጋር በተያያዘ ክለቦች ወደ ካዝናቸው ገንዘብ ማስገባት ቢጀምሩም አሁንም ከጠቅላላ ወጪያቸውን አንፃር ሰፊ የሆነ የወጪ እና ገቢ ልዩነት ይታይባቸዋል ። በሀገራችን ያለው የእግርኳስ ክለብ መዋቅር አነስተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የእግርኳስ ክለቦቻችን መሰረታዊው እና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ለተጫዋቾች ዝውውር እና ደሞዝ የሚያወጧቸው ወጪዎች መሆናቸው እርግጥ ነው። በመሆኑም በርካታ ክለቦች “እግርኳሳዊ ባልሆነ የፉክክር መንፈስ” ከዓመት ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ማድረግ የተለመደው አካሄድ የበርካታ ክለቦችን ህልውና ወደ መገዳደሩ መጥቷል።
ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅምችን በወቅቱ ለመክፈል የመቸገር ጉዳይ ርዕሰ ዜና መሆኑ ቀርቶ እንደ መደበኛ ጉዳይ መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል። በመሆኑም ይህን ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስም ሆነ የክለቦችን ህልውና ዘላቂ ለማድረግ የክለቦችን የገንዘብ አወጣጥ ላይ ገደብ የሚጥሉ አስገዳጅ ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ የግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ደርሰናል።
የአውሮፖ እግርኳስ ማህበር ከዓመታት በፊት ተግባራዊ ያደረገው የክለቦች የፋይናንስ ጨዋነት ደንብ /FFP/ እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በራሱ አውድ አሻሽሎ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የሊጉ ክለቦች ትርፋማነት እና ቀጣይነት ህግ ዓይነት የክለቦችን የወቅቱን የሂሳብ መዝገብ ጨምሮ ወደ ኋላ ያሉ ሁለት የበጀት ዓመታትን የሂሳብ መዝገብ በመመርመር የኪሳራ መጠናቸው ላይ ጣራ በማስቀመጥ አለፍ ሲልም ደግሞ ይህን መጠን አልፈው የሚገኙ ክለቦች ላይ ጠንከር ያሉ ቅጣቶችን በመጣል በተወሰነ መልኩ ልቅ የወጣውን የክለቦች የፋይናንስ አጠቃቀም ላይ ልጓም ካልተበጀ የክለቦቻችን ቀጣይነት አደጋ ላይ ወድቋል።
ይህ ሂደት እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል የሚለው ጉዳይ በጥናት የሚመለስ ቢሆንም የሊጉን የፉክክር ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ ጠንካራ ሊግ ለመገንባት አለፍ ሲልም ግዙፉ እግርኳሳዊ “ኩባንያዎችን” ለመመልከት ክለቦች ከዕለት ተዕለት ወጪዎች ባለፈ ዘለቄታ ባላቸው መስኮች ላይ ያላቸውን መዋዕለንዋይ እንዲያፈሱ ለማድረግ ይህ የፋይናንስ ስርአትን የሚቆጣጠር ደንብ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለም።
👉 አይደክሜው ሀዋሳ ወደ ላይ እየተጠጋ ይገኛል
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን የረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 23 በማሳደግ በሊጉ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል።
በወጣቶች የተገነባው ቡድኑ ባለፉት ዓመታት የዚህን ትሩፋት (Competitive Advantage) በመጠቀም ረገድ ብዙም አመርቂ አፈፃፀምን ለማሳየት የተቸገረ ቡድን መሆኑን ስንመለከት ብንቆይም ዘንድሮ ግን ከዚህ በተሻለ ይህን እውነታ ወደ ሜዳ ለማውረድ እየተጋ ይገኛል።
ለአብነትም ቡድኑ በሊጉ እስካሁን ካስቆጠራቸው አስራ ስድስት ጎሎች ውስጥ አስሩ በሁለተኛ አጋማሽ የተገኙ ሲሆን በሁለተኛ አጋማሽ ከተቆጠሩት አስር ጎሎች ደግሞ አራቱ በመጨረሻ አምስት እና ስድስት ደቂቃዎች መረብ ላይ ያረፉ መሆናቸው ቡድኑ በወጣቶች እንደመገንባቱ አይደክሜ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ሌላኛው ከቡድኑ ጋር የሚነሳው ጉዳይ ከጨዋታ ጨዋታ ተለዋዋጭ ባህሪን መላበሱ ነው ፤ በዚህም ቡድኑ ተጋጣሚን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በየጨዋታው እንደሚያደርግ ይታያል።
በመጨረሻው የፋሲል ከነማ ጨዋታ የተጫዋቾች እና የአደራደር ለውጥ በማድረግ በ3-5-2 አደራደር ሲጀምሩ የተለያዩ ለውጦችን አድርገው ነበር። ለአብነትም በሚና ረገድ ወንድማገኝ ኃይሉ ከቀደሙት ጨዋታዎች በተለየ ወደ ኋላ ተጠግቶ እንዲጫወት የተደረገ ሲሆን እንዲሁም ኤፍሬም አሻሞ ደግሞ ከመስመር ተጫዋችነት ይልቅ ወደ መሀል አጥብቦ በአማካይ መስመር ላይ እንዲጫወት ሆኗል።
ይህ የሆነው ደግሞ የፋሲልን የአማካይ መስመር የኳስ ብልጫን እንዳይወስድ ለማድረግ በማሰብ ነበር። ከዚህ ውጪም ለውጦቹም የተጋጣሚን የመስመር ላይ ጥቃቶችን ለመመከት በማሰብ የተተገበረ ነው። ለዛም ይመስላል ፋሲል ሁለቱንም የመስመር ተመላላሾች የቀየረው (አንዱ በአስገዳጅ ጉዳት ቢሆንም) በተመሳሳይ ፈጣሪ አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸውንም ገና በሙሉ ሰዓት አካባቢ ነበር የለወጠው።
በተያያዘም የቡድኑ የፊት መስመር ፍጥነት እና ስልነት አድናቆት የሚቸረው ነው። ሀዋሳ በአጠቃላይ በእስካሁኑ የውድድር ዘመን ጉዞ ካስቆጠራቸው 16 ጎሎች ላይ የቡድኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ የሆኑት ኤፍሬም አሻሞ ፣ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ በ13ቱ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ (በማስቆጠርም ሆነ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል) አድርገዋል። በተቆጠሩ ግቦች ብቻም ከተመለከትን እንደዚሁ ሦስቱ አጥቂዎች ከ16ቱ 11ዱን (68.75%) አስቆጥረዋል።
አሁን ላይ በ23 ነጥቦች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ነጥቦች ርቆ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ምናልባት የብዙዎችን ግምት በማፋለስ ለሊጉ ክብር በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ኮስታራ ሆኖ ይዘልቃል ወይ የሚለው ጉዳይ ይህንን መልካም አቋም በወጥነት ማስቀጠሉ ላይ የሚወሰን ይሆናል።
👉 ኢትዮጵያ ቡና – የውድድር ዓመቱ ደካማ እንቅስቃሴ
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመጀመሪያ ሙሉ የውድድር ዘመን ፋሲል ከነማን ተከትለው ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዘንድሮ በብዙዎች ዘንድ ለዋንጫ ቢታጩም አሁን ላይ እየተጓዙበት ያለው አዝማሚያ ስጋት የሚፈጥር ነው።
ወልቂጤ ከተማን በ8ኛው የጨዋታ ሳምንት ከረታበት ጨዋታ ወዲህ ቡድኑ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች ማሳካት የቻለው አራት መሆኑ የቡድኑን ሰሞነኛ አቋም የሚገልፅ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ በተሸነፈበት ጨዋታ ያሳየው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በካሳዬ አራጌ ዘመን ከተመለከትናቸው የኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ደካማው ነበር ብንል ማጋነን አይሆንም።
እንደየትኛውም በኳስ ቁጥጥር መጫወትን ለሚሻ እና ኳሶች ከራሱ የግብ ክልል መስርቶ መውጣት የሚፈልግ ቡድን ሁለቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚሆኑት በምስረታ ወቅት ተጋጣሚ ጫና ለማሳደር ቢመጣ በምን መልኩ ይህን ጫና በማለፍ ኳሱን ማሳደግ ይቻላል የሚለው ጉዳይ አንደኛው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኳስ ቅብብሎችን እንዴት አደጋ ወደ ሚፈጥሩ ቦታዎች ማድረስ እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል የሚሉት ጥያቄዎች በቀዳሚነት መልስ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ረገድ በጫና ውስጥ የመመስረትም ሆነ ኳሶችን በመቀባበል እድል ለመፍጠር ፍላጎት ያለው ቡድን ቢሆንም በሁለቱም መመዘኛዎች ላይ የአማራጭ ሀሳቦች እጥረት እንዳለበት እየተመለከትን እንገኛለን።
በአርባምንጩ ጨዋታ ገና ከጅምሩ አርባምንጮች እጅግ በተጠና መልኩ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን በራሳቸው ደጃፍ ላይ ጫና ውስጥ ለመክተት ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል። የአርባምንጭ ከተማ ከሌሎች ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥሙ ጫና ለማሳደር ፈልገው ወደ ሜዳ ከሚገቡት ቡድኖች በተወሰነ መልኩ የተለየ እና የተቀናጀ ማለትም ኳስ የያዘውንም ሆነ ኳሱን ሊቀበሉ የሚችሉ አማራጭ ተጫዋቾችን ሰው በሰው ጫና እንዲያድርባቸው በማድረግ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ለኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን እጅግ አስቸጋሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
እጅግ አስደናቂ የጫና አፈፃፀም የነበራቸው አርባምንጭ ከተማዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ተደጋጋሚ ኳሶችን መንጠቅ (Turnover) ቢችሉም ለወትሮም ቢሆን የጥራት ጥያቄ የሚነሳበት የቡድኑ የአጥቂ መስመር ብኩነት ሆነ እንጂ ጥራት ያላቸው አጥቂዎች ቢኖራቸው አራት እና አምስት ግቦችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር።
አቡበከር ናስርን በመጀመሪያ ተመራጭነት ሳይዝ የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና (በ63ኛ ደቂቃ ተቀይገሮ ገብቷል) በሙሉ ዘጠና ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድም ኢላማውን የጠቀ ሆነ ያልጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችል የቀረ ሲሆን በጨዋታ ሂደት በራሳቸው ሜዳ ተደጋጋሚ ኳሶችን ቢነጠቁም እንደወትሮው ሁሉ ኃላፊነት ወስደው ጨዋታውን በጀመሩበት መንገድ ለመቀጠል ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም መጠነኛ ማስተካከያዎችን ሳያደርጉ የመዝለቃቸው ነገር ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው።
ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከወዲሁ በ11 ነጥቦች ርቀው በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ፉክክሩ ለመመለስ ከፍተኛ የቤት ስራ የሚጠብቃቸው ሲሆን በፍጥነት ወቅታዊ አቋማቸውን ማስተካክል የማይችሉ ከሆኑ ከዋንጫ ፉክክሩ የመውጣታቸው ነገር የሚቀር አይመስልም።
👉 የፋሲል ከነማ መንሸራተት
የአምና የሊጉ አሸናፊ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ዘንድሮ ግን በቀደመው የጥንካሬ ደረጃቸው ለመዝለቅ ተቸገረው እየተመለከትን እንገኛለን። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ የተሸነፈው ቡድኑ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ይገኛል።
ከአሸናፊነት በኋላ በሚኖረው የውድድር ዘመን አሸናፊው ቡድን በብዙ መንገዶች የትኩረት ማዕከል እንደሚሆን ቢጠበቅም ቡድኑ ከዚህ ሁኔታ ጋር የተስካከለ ዝግጅትም ሆነ ወቅታዊ ቁመና ላይ አይገኝም።
ከፋሲል ከተማ የቁልቁለት ጉዞ ጋር በርካታ ጉዳዮችን በምክንያትነት ማቅረብ ቢቻልም መሰረታዊው ጉዳይ ግን አሰልጣኙን እና ተጫዋቾቹን በቀጥታ የሚመለከቱ ናቸው። ተጫዋቾቹን በተመለከተ የሚነሳው ቀዳሚው ጉዳይ የሚሆነው የተጫዋቾች የአቋም መውረድ ጉዳይ ነው።
ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ባሉት የመጫወቻ ስፍራዎች ላይ ከዚህ ቀደም በምናውቀው የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኝ ተጫዋች አለ ብሎ ለመጥቀስ እሰከሚያስቸግር ድረስ አብዛኛዎቹ የቡድኑ ተጫዋች ወቅታዊ አቋም ለማመን በሚያስቸግር ደረጃ ወርዶ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህም እንደ አጠቃላይ ደግሞ ቡድኑ በማጥቃትም ሆነ በመከላከሉ ፍፁም ተዳክሞ እንዲቀርብ ያስገደደ ሆኗል።
ሌላኛው ጉዳይ ከባለፉት ጥቂት ዓመታት አንስቶ በሊጉ እጅግ የተረጋጋ ስብስብ እንደሆነ የሚነገርለት የፋሲል ከነማ ስብስብ በየዓመቱ የቡድኑን ዕድገት በማይጎዳ መልኩ የስብስብ ጥራት ደረጃ ለማሳደግ የሚረዱ የተመረጡ ዝውውሮችን በመፈፀም የመጡትም ተጫዋቾች በፍጥነት ተዋህደው ቡድኑን በማሳደግ ረገድ ከፍ ያለ ድርሻ ሲወጡ ተመልክተናል። ነገር ግን የዘንድሮ ዝውውሮቹ ያንን ለማድረግ ተቸግረው እየተመለከተን እንገኛለን።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ዓመታት ወጥ የመሀል ተከላካይ ጥምረትን የፈጠሩትን የያሬድ ባየህ እና አስቻለው ታመንን በክለብ ለመመልከት እንዲጓጉ ያደረገው የአስቻለው ታመነ የፋሲል ከነማ ዝውውር እስካሁን በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ ለመሆን ተቸግሯል። ይልቁኑም በአንዳንድ አጋጣሚ ቡድኑ ለተቆጠሩበት ግቦች መንስኤ ሲሆን ተመልከተናል።
በተመሳሳይ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ፈረሰኞቹን ለቆ አፄዎቹን የተቀላቀለው አብዱልከሪም መሀመድ ከአንድ ጨዋታ የዘለለ አበርክቶ ለቡድኑ መስጠት ሳይችል ቀሪ የ18 ወራት ውል ከቡድኑ ጋር እየቀረው በስምምነት ከቀናት በፊት ተለያይቷል።
በፊት መስመር እንዲሁ ወደ አልጄሪያ አቅንቶ በነበረው እና ባለፉት ዓመታት የቡድኑ ሁነኛ የግብ አስቆጣሪ የነበረውን ሙጂብ ቃሲምን ለመተካት በሊጉ ጥሩ የአስቆጣሪነት ታሪክ ያለውን ግዙፉ ናይጄሪያ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢን ቢያስፈርሙም ብዙ ተጠብቆበት ፋሲል የደረሰው ኦኪኪ እስካሁን ሁለት ግቦችን ብቻ ነው ያስቆጠረው።
በተጨማሪም ብዙዎች አሰልጣኙ ይህን መንሸራተት ለመቀልበስ እያደረጉ የሚገኙት ጥረት እንዲሁም በዚህ ደረጃ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ብቃት መውረዱን ከአሰልጣኙ የስልጠና መንገድ እና የቡድኑን መልበሻ ክፍል እየመሩበት የሚገኘው መንገድ ላይ እንዲሁ ጥያቄዎች ለማንሳት ያስገድዳል።
ፋሲል ከነማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈትን ቢያስተናግድም አሁንም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምስት ነጥቦች ርቀው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም አሁን ላይ ጊዜ ያልረፈደ ቢሆንም በፍጥነት ነገሮች ወደ መስመር መመለስ በክለቡ ዙርያ የተሰባሰቡ አካላት በሙሉ የጋራ የቤት ሥራ ነው።
👉 ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡ ወደ ሁለት አሀዝ ደርሷል
ከጅማሬው አንስቶ በሊጉ ግርጌ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር አሁን ላይ ግን ነጥቡን አስር አድርሶ ወደ 15ኛ ደረጃ ፈቀቅ ብሏል።
ፕሪሚየር ሊጉ ወደ ድሬዳዋ ካቀና ወዲህ ሜዳ ላይ ነገሮች አልጋ በአልጋ እየሆኑላቸው የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች አንድ ነጥብ ላይ ረግተው የነበረ ቢሆንም በድሬዳዋ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን በማሸነፍ በዚህ ፍጥነት የነጥብ ብዛታቸውን ወደ ሁለት አሀዝ በማሳደግ ከሊጉ ግርጌ ለመላቀቅ በቅተዋል።
ነገሮች ጥሩ ባልነበሩባቸው ጊዜያት እንኳን ከተጋጣሚዎቹ ጋር በኳስ ቁጥጥር ለመገዳደር ይፈልግ የነበረው ቡድኑ አሁን ግን ኳስ ከመቆጣጠር ባለፈ የተሻለ የመልሶ ማጥቃት ቡድን ወደመሆን እንደመጣ እንደሆነ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በግልፅ እያስመለከቱን ይገኛሉ። በተለይም ሆሳዕናን በረቱበት እና በዚህኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ባሸነፉበት ወቅት የተቆጠሩት ግቦች የዚህ ሂደት ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው።
በመልሶ ማጥቃት የሰላ ለመሆነ እየተጋ የሚገኘው ቡድኑ ከኋላ በባልምዶቹ ዳዊት እና መስዑድ ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ ከፊት የእዮብ አለማየሁ እና መሀመድ ኑር ናስርን ፍጥነት በመጠቀም ጥቃቱን ቅርፅ እያስያዘ ይገኛል።
አሁን ላይ በ10 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ እስከ 12ኛ ደረጃ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ስድስት ደርሷል። በመሆኑም ይህን ሰሞነኛ መነቃቃት ማስቀጠል ከቻለ ምናልባት የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ከወራጅ ቀጠናው በተወሰነ መልኩ ከፍ ብለው ሊቀመጡ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን አሁንም ሊፈታ ያልቻለው እና በዚህ ሳምንትም ተጫዋቾች ልምምድ እንዲያቋርጡ ያስገደደው የደመወዝ ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት የግድ የሚል ይሆናል። ሜዳ ላይ ቡድኑ ያሳየው መነቃቃት ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች ምክንያት ከስሞ ዳግም የውጤት ቀውሱ እንዳይቀጥል የክለቡ አመራሮች ፈጣን እርምጃ ይጠበቃል።