[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በሦስተኛው ፅሁፋችን ለመዳሰስ ተሞክሯል።
👉 የተመስገን ዳና የመጀመሪያ ጨዋታ
ከቀናት በፊት ወልቂጤ ከተማን የተረከቡት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሊጉ በዋና አሰልጣኝነት በመሩት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሲዳማ ቡና ጋር በአቻ ውጤት ቢደመድምም በእንቅስቃሴ ረገድ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ ተስፋ የሚሰጡ ሂደቶችን አስመልክቶናል።
በተለይ ኳስን ለመቆጣጠር ሆነ አጥቅቶ ለመጫወት የተመቹ በርካታ ተጫዋቾችን እንደመያዙ በሚፈለገው ደረጃ ጨዋታን በመቆጣጠር እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነቶች የነበሩበትን ስብስብ የተረከቡት አሰልጣኙ በጥቂት ቀናት ልምምዶች ቡድኑን ከቀደመው ጊዜ በተሻለ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ነበሩ።
እንደ አብዛኞቹ አሰልጣኛቸውን በውድድር መሀል እንደሚቀይሩ ቡድኖች ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታቸውን ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች ከወትሮው በተለየ ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ተጠግተው ተጋጣሚን ጫና ውስጥ በመክተት ፈጠን ባሉ ቅብብሎች ወደ ሳጥን ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።
እርግጥ የመጀመሪያ ጨዋታ ቢሆንም የተመለከትናቸው ተስፋ ሰጪ የጨዋታ ቅንጣቶች በቀጣይ ከቡድኑ ብዙ እንድንጠብቅ የሚያስገድዱ ናቸው። በሁለተኛው አጋማሽ ግን አሰልጣኙ ራሱ ከጨዋታ በኋላ እንዳረጋገጡት በተለይ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎቻቸው የማስጠንቀቂያ ካርዶችን በመመልከታቸው በእሳቸው ትዕዛዝ ለአካላዊ ንኪኪ ይዳርጋል ባሉት ከፍ ያለ ጫና አሳድሮ የመጫወት መንገድ ስላለመቀጠላቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከሞላ ጎደል ግን ቡድኑ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ያሳየን የጨዋታ መንገድ አሰልጣኙ ይበልጥ ከቡድኑ ጋር እየተላመዱ እና ተደጋጋሚ የልምምድ ጊዜያትን ከተጫዋቾቻቸው ጋር ሲያሳልፉ በጣም ለማየት የሚያጓጓ ቡድን ሊሆን እንደሚችል እንድንገምት ያደረገን የጨዋታ ጊዜ አሳልፈዋል።
👉 የዘላለም ሽፈራው እና የሰበታ መጨረሻ የቀረበ ይመስላል
በክረምቱ የዝውውር መስኮት በወላይታ ድቻ ውላቸውን ያራዝማሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሳይጠበቅ በሦስት ዓመት የውል ስምምነት ሰበታ ከተማን እንደተረከቡ አይዘነጋም።
ቡድኑ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገበት ወቅት አንስቶ ይበልጥ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ በሚሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አብርሃም መብራቱ ምስል ተገንብቶ የነበረው ስብስቡ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሌላ መልክ እንዲይዝ በርካታ ዝውውሮችን መፈፀሙ አይዘነጋም።
ታድያ በዚህ ሁኔታ የውድድር ዘመኑን የጀመሩት አሰልጣኙ የገነቡት ቡድን እሳቸው ተራቀውበታል በሚባሉበት የመከላከል ጨዋታ በአግባቡ ለመከላከል የማይችል ወደ ማጥቃቱ ሲሸጋገር ደግሞ ሀሳቦች ፍፁም የሚያጥሩት ቡድን እንደሆነ የ13 ሳምንታት የቡድኑ ጉዞ በግልፅ የሚያሳየው እውነታ ነበር።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አሰቃቂ የሆነ 5-1 ሽንፈት ያስተናገደው ሰበታ በ7 ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ሲገኝ በሊጉ ከፍተኛ የሆነውን 23 ግቦች ሲያስተናግድ በአስቆጠራቸው ግቦችም መጠንም እንዲሁ ከዝቅተኞቹ ተርታ የሚመደብ ነው።
በዚህ የውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አሰልጣኙ በአዲስ አበባ ከተሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ከአስር የሚልቁ የቡድኑ ተጫዋች ከ2013 አንስቶ ያልተከፈላቸው ደመወዝ ስለመኖሩ በይፋ ሲናገሩ ተደምጠዋል። በዚህ ሂደት ውጥረት ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኙ ከሰበታ ከተማ ጋር የመቆየታቸው ነገር ያበቃለት ጉዳይ መስሏል።
👉 የዮሐንስ ሳህሌ አስተያየት
መከላከያን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በወጣቶች ላይ ያላቸው ዕምነት ከብዙዎቹ አሰልጣኞች በልዩነት የሚጠቀስላቸው ጥንካሬ እንደሆነ ይታመናል። አሰልጣኙ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ካደረገው ጨዋታ አስቀድሞ ጠንከር ያለ ይዘት ያለውን ሀሳብ ሲሰጡ ተደምጠዋል።
አሰልጣኙ በቅድመ ጨዋታ ቃለ መጠይቃቸው ወቅት ልምድ ስላላቸው ተጫዋቾች እና ስለወጣት ተጫዋቾች ልዩነት ሲያብራሩ ወጣት ተጫዋቾችን ዕድል በመስጠት ውስጥ ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ ባለ ልምድ ተጫዋቾች ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው ተጫዋቾች ለቡድን በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንጂ በሊጉ ብዙ ዓመት በመጫወታቸው ብቻ ሊመዘኑ እንደማይገባ ተናግረዋል።
ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ የመጡት ቡድኖች በተወሰነ መልኩ ይህን እሳቤ ሰበሩ እንጂ በቀደሙት ዓመታት ወደ ሊጉ የሚመጡ ቡድኖች በተለይ በሊጉ የመጫወት ልምድ አላቸው ለተባሉ ተጫዋቾች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ወደ ቡድኖቻቸው በብዛት ለማዘዋወር ሲጥሩ ይታያል። ነገር ግን ይህ አካሄድ እምብዛም ውጤታማ ሲያደርጋቸው አይስተዋልም። ታድያ አሁን ላይ ግን መከላከያን ጨምሮ አንዳንድ ክለቦች ከዚህ ልምድ ላይ ብቻ ትኩረት ከሰጠ አካሄድ ወጥተው የቀደመ ስብባቸውን የማስቀጠል ፍላጎት ሲያሳዩ እየተመለከትን እንገኛለን።
በመሆኑም በሊጉ ብዙ ዓመት ስለተጫወቱ ብቻ በስም የምናውቃቸውን ተጫዋቾች ለማዘዋወር ከመሽቀዳደም ይልቅ ወጣት ተጫዋቾችን በሊጉ የመጫወት ልምድ ያላቸው በተጨማሪም በነበራቸው ቆይታ የተሻለ አበርክቶ ለቡድናቸው መስጠት የቻሉ ተጫዋቾችን ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ መልምሎ ሁለቱን አጣምሮ መጓዝ የተሻለው አማራጭ ስለመሆኑ አሰልጣኝ ዮሐንስ አስረግጠው ተናግረዋል።