ጋናዊው የመስመር አጥቂ ከሰበታ ጋር ልምምድ ጀምሯል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከአሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው ጋር ከሰሞኑ ሰጣ ገባ ውስጥ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ሁለተኛውን የውጭ ዜጋ ተጫዋች ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ወደ ቡድኑ አምጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያልተሳካ የውድድር አመትን በ13ቱ የሊጉ ሳምንታት ያሳለፈው ሰበታ ከተማ ከሰሞኑ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባ ሲሆን አሰልጣኙም ከክለቡ ጋር የተፈጠረው ጉዳይ አግባብ አደለም በማለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ቅሬታን በደብዳቤ ገልፀው ከትላንት በስቲያ አስገብተዋል፡፡ነገ በ14ተኛ ሳምንት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን በረዳት አሰልጣኝነት ረጅም አመት ክለቡን በመምራት ያሳለፉት እና ለቀናቶች ከክለቡ ታግደው በነበሩት አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ከቀናቶች በፊት ዩጋንዳዊውን አጥቂ ኤሪክ ኒሲሲንባን በነፃ ዝውውር ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለተኛው የውጪ ዜጋ ተጫዋች ለማስፈረም በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ጋናዊው የመስመር አጥቂ ቢስማርክ አፒያ ወደ ኢትዮጵያ ዳግም መጥቶ ከሰበታ ከተማ ጋር ልምምድ ጀምሯል፡፡ የቱኒዚያውን ክለብ ለቆ 2010 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በጅማ አባጅፋር ፣ ስሑል ሽረ እና ባለፈው አመት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሰነበተው ተጫዋቹ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የነበረው የደመወዝ ክርክር በፊፋ ጉዳዩ የተያዘ ቢሆንም ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ ከሰባት ወራት በኋላ ተመልሶ ትሪያልንግል ሆቴል የሚገኘውን ሰበታ ከተማን ለመቀላቀል ከክለቡ ጋር ዝግጅት የጀመረ ሲሆን የዝውውር መስኮቱ በቅርቡ ሲከፈት የሰበታ ከተማ ተጫዋች በይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡