​ስሑል ሽረ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በ2017 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ የሆነው ስሑል ሽረ አዲስ አሰልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከአራት ዓመታት በኋላ ዳግም የሚሳተፈው ስሑል ሽረ ቡድኑን በአሰልጣኝነት የሚመራ አሰልጣኝን በሀላፊነት ስለ መሾሙ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ የደረሳት መረጃ አመላክቷል። ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት የተረከቡት ደግሞ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ሆነዋል።

መቐለ 70 እንደርታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ የሚታወቁት እና በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፣ ደደቢት ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና አክሱም ከተማን ከዚህ ቀደም የመሩት አሰልጣኙ ከትግራዩ ጦርነት በኋላ በያዝነው ዓመት ለስድስት ወራት ያህል ወሎ ኮምቦልቻን በከፍተኛ ሊጉ ማሰልጠኛቸው የሚታወስ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ ስሑል ሽረን በፕሪምየር ሊጉ እያሰለጠኑ ለመቆየት ክለቡ ሾሟቸዋል።