​ምዓም አናብስት  በይፋ አሰልጣኝ ቀጥረዋል

ዳንኤል ፀሐዬ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ ወደ መቐለ ተመልሷል

ከቀናት በፊት ዳንኤል ፀሐዬ የመቐለ 70 እንደርታ አሰልጣኝ ለመሆን መቃረቡን መግለፃችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ ክለቡ ይፋ ባደረገው መሰረት አሰልጣኙ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ቡድኑን ለመረከብ ፊርማውን አኑሯል። በተጫዋችነት ሕይወቱ መባቻ ላይ በመጨረሻዎቹ ዓመታት በመቐለ ከተማ አስተዳደር ስር ሲተዳደር በነበረውና ስሙን ከጉና ንግድ ወደ መቐለ ከተማ በመለወጥ ሲወዳደር በነበረው ያሁኑ መቐለ 70 እንደርታ በቡድን መሪነትና በተጫዋችነት ያገለገለው ዳንኤል ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ በአዲስ ሞያ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል። 

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በጉና ንግድና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የቻለው የቀድሞ አጥቂ ወደ አሰልጣኝነት ሞያ ከገባ በኋላ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ምክትል አሰልጣኝ፤ በደደቢት የታዳጊና የዋናው ቡድን አሰልጣኝ፤ በስሑል ሽረ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደጉ ሲታወስ ባለፈው የውድድር ዓመትም በመቻል የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ምክትል ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል። 

በተያያዘ ዜና መቐለ 70 እንደርታ ቀደም ብሎ በሐምሌ ወር አጋማሽ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል።