ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን እናነሳለን።

👉 የረዳት ዳኞቻችን ስህተቶች መበራከት

የዲ ኤስ ቲ ቪ ወደ ሀገራችን እግርኳስ መምጣት ከበርካታ ነገሮች አንፃር የጠራ ዕይታ እንዲኖረን እያደረገ ይገኛል። የቡድኖችን እና የተጨዋቾችን የተናጠል ብቃት በተሻለ መረዳት ለመግምገም ማስቻሉ እንዳለ ሆኖ የዳኝነት ውሳኔዎችንም በድጋሚ የምስል እይታዎች በግልፅ ለማስተዋል የቴሌቪዢን ሽፋኑ ትልቅ እገዛን አድርጓል። ከዚህ አንፃር በቁጥር ቀላል የማይባሉ የዳኝነት ስህተቶችን በተለያዩ የውሳኔ ዓይነቶች ተመልክተናል። የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄዎች ፣ ካርድ የሚያስመዝዙ ክስተቶች ፣ የሜዳውን መስመሮች የተሻገሩ ኳሶች ፣ ከእንቅስቃሴ ውጪ የሚሰሩ ጥፋቶች የመሳሰሉት በዚህ ውስጥ ሲካቱቱ የጨዋታ ውጪ ውሳኔዎች ደግሞ ከሁሉም በላይ ትኩረት ሳቢዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

በዋነኝነት በረዳት ዳኞች ውሳኔ የሚሰጥባቸው የጨዋታ ውጪ ሂደቶች በባህሪያቸው ቅፅበታዊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚወሰኑ መሆናቻው የዳኞችን አካላዊ እና አዕምሯዊ ፍጥነት ይጠይቃሉ። በእርግጥ የVAR ቴክኖሎጂ ችግሩን ማቃለል ቢችልም በእኛ ብቻ ሳይሆን በዘመነው የእግርኳስ ዓለምም በመሰል ውሳኔዎች ላይ ስህተቶች ሲፈጠሩ ይታያል። ለዚህ ያልታደለው የእኛው እግርኳስ ላይ ግን ችግሩ መታየቱን ሲቀጥል ጨዋታዎች በቴሌቪዥን ሽፋን ማግኘት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ያስተዋልነው የረዳት ዳኞቻችን ስህተቶች ብዛት ግን የእስካሁኑን የእግርካሳችንን ውጤት እንድንጠራጠር ሁሉ የሚያደርጉን ናቸው።

በተለይም በዘንድሮው የውድድር ዓመት ነገሩ ግድ እስኪመስል ድረስ በየጨዋታው ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የተዛቡ የጨዋታ ውጪ ውሳኔዎች ተደጋግመው ሲሰጡ ተስተውሏል። አጋጣሚዎቹ ውጤት ቀያሪ የመሆናቸው ወይንም ወደ ግብነት ተለውጠው መታየታቸው ውሳኔዎቹን የሚያከብድበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችልም ምልክት ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህ ሳምንት ከፍተኛ መነጋገርያ የነበረው በወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል በተደረገው ጨዋታም የወልቂጤ ከተማው አማካይ በኃይሉ ተሻገር ከግሩም ቅብብል በኋላ ያስቆጠራትን ግብ የዕለቱ ረዳት ዳኛ ዳንኤል ጥበቡ ከጨዋታ ውጪ በማለት እንዳይፀድቅ ያደረገበት ነበር። ይህች ጎል ብትፀድቅ ኖሮ 0-0 የተጠናቀቀው ጨዋታ ሌላ መልክ እንዲኖረው የሚያስችል ከመሆኑ አንፃር መነጋገርያ ሆኗል።

ይህ ተደጋጋሚ ስህተት ክለቦችን ውጤት ከማሳጣት አልፎ ዓለም በሚያያቸው ጨዋታዎች ሊጉን ለትዝብት የሚዳርግ በመሆኑ በውድድሩ ድምቀት ላይ ጥላ ካጠሉ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል። ይህም ሳይወል ሳያድር በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ እና በጨዋታ አመራሮች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

👉 አርቢትር በላይ ታደሠ እና ግርማ ዲሳሳ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ስድስተኛ ጨዋታቸውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ሁለተኛ ቀይ ካርዳቸውን በተመሳሳይ ተጫዋች ላይ የመዘዙበት አጋጣሚ በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትናቸው አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ነበር።

ባህር ዳር ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ ባገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ አንደኛው መርሐግብርን በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር በላይ ታደሰ ከዚህ በፊት በመሯቸው ጨዋታዎች 22 ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ መዘው የነበሩት ሲሆን ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ባህር ዳር ከተማን ከአዳማ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የባህር ዳሩ የመስመር ተጫዋች ግርማ ዲሳሳ ላይ የመጀመሪያ ቀይ ካርዳቸውን መምዘዛቸው አይዘነጋም።

ታድያ ተጫዋቹ በተመለከተው ቀይ ካርድ መነሻነት ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎችን በቅጣት መሰለፍ ሳይችል ቆይቶ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዳግሞ ወደ ጨዋታ በተመለሰበት እና ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በሰራው ጥፋት ጨዋታውን በመሩት እና ከሳምንታት በፊት በቀይ ያሰናበቱት አልቢትር በላይ ዳግም በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊያሰናብቱት ችለዋል።

👉 ብዙም ያልተለመዱት የውሰት ዝውውሮች

የዝውውር መስኮቶች በተከፈቱ ቁጥር በሀገራችን እግርኳስ የተለመደው አካሄድ ለአንድ አለፍ ሲል የሁለት ዓመት ርዝማኔ ያላቸው ቋሚ ዝውውሮችን መፈፀም የተለመደ አካሄድ ሲሆን ከዚህ ውጭ ያሉ የዝውውር አማራጮች ግን በስፋት ሲተገበሩ አይስተዋልም።

በተለይውም ደግሞ የውሰት ዝውውሮች በሀገራችን እግርኳስ ክለቦች መካከል ሲደረጉ እምብዛም አይስተዋልም። ነገር ግን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጅማ አባ ጅፋር መሰል ዝውውሮችን ፈፅሞ ተመልክተናል።

የዘንድሮው ውድድር ከተጀመረ በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች በመጀመሪያ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በተመለከቷቸው ክፍተቶች መነሻነት አራት ተስፈኛ ተጫዋቾች በውሰት ውል ማስፈረማቸው አይዘነጋም። ግብጠባቂው አላዛር ማርቆስ (ከሀዋሳ) ፣ ብሩክ አለማየሁ (ከሀዋሳ ከተማ) ፣ ምስጋናው መላኩ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ትንሳኤ ይርጌሳ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ) ማስፈረማቸው ይታወሳል።

ታድያ ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል በተለይ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ለቡድኑ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። ጅማ በዚህኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ሙሉ ሦስት ነጥብ ሲነጥቅ የተጫዋቹ አበርክቶ ከፍ ያለ ነበር። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ይህን ብለዋል።

“…እኛ ላይ ብዙ ጎሎች ተሞክረዋል። ለዚህ ደግሞ የታዳጊው ግብ ጠባቂያችን አስተዋፅዖ ትልቅ ዋጋ ነበረው። በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግነው አላልፍም። ይህንን ዕድል ያመቻቸልኝ ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ነው። ወጣቶችን ለማምጣት ሳስብ ቦርዱ ሙሉ ነፃነት ነው የሰጠኝ። ለሀገርም ተስፋ የሚሰጥ ነው። በዚህ አጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ወጣቶችን ስለሰጡን እግረ መንገዴን ሳላመሰግናቸው አላልፍም።”

የውሰት ዝውውሮች ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ሁለቱ ክለቦች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል የሚሰጥ ነው። በውሰት ተጫዋቹን የሚሰጠው ክለብ ከዕድሜ እርከን ቡድኖች ያደጉ አልያም በዝውውር መጥተው በሚፈለገው ደረጃ በዋናው ቡድን ራሳቸውን ማደላደል ያልቻሉ ተጫዋቾች በሌላ ከባቢ ራሳቸውን መልሰው እንዲያገኙ ዕድል የሚያስገኝ ሲሆን በተቃራኒው ተጫዋቹን የሚያገኘው ቡድን ደግሞ አፈጣኝ መልስ ለሚሹ ጥያቄዎቹ ምላሽ የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር የዝውውር አይነት ነው። በመሆኑም በሊጉ መሰል ዝውውሮች ይበልጥ እየተለመዱ መምጣት ይኖርባቸዋል።

👉 የግቦች መቀነስ

ከ10ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ውድድሩን እያስተናገደ የሚገኘው ድሬዳዋ ዓለምዓቀፍ ስታዲየም በርካታ ግቦች በጨዋታዎችን ሲያስመለክተን ቢቆይም አሁን ግን ግቦቹ እየደረቁ መጥተዋል።

በ10ኛ እና 11ኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች በድምሩ 19 እና 25 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን በቀጣይ በነበሩት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት የተቆጠሩ የግብ መጠኖች ግን ከፍተኛ ቅናሽ በማሳየት 13 እና 12 የመሆናቸው ጉዳይ በጣም የሚያነጋግር ነው።

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት አንድ ጨዋታ ብቻ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በ13ኛ የጨዋታ ሳምንት ግን ሦስት ጨዋታዎች በ0-0 ውጤት ተጠናቀዋል። በመሆኑም ቀስ በቀስ የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቂያም እየተቃረበ እንደመምጣቱ ላለመውረድ እና ለዋንጫ በሚደረገው ፉክክር ቀጥተኛ ተፎካካሪ ቡድኖች እየተለዩ ከመምጣታቸው ጋር ተዳምሮ ቡድኖች ይበልጥ በ ኃላፊነት ጨዋታዎችን በጥንቃቄ መጫወትን እየመረጡ ይሆን ?

ያጋሩ