ቢጫዎቹ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከጫፍ ደርሰዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጣዩ ዓመት ተሳታፊ የሆነው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ተቃርቧል።

ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በዝግጅት ላይ የቆዩት ወልዋሎዎች ላለፉት ሳምንታት በርከት ያሉ አሰልጣኞች ሲመለከቱ ከቆዩ በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ለመሾም መቃረባቸው ለማወቅ ተችሏል። ክለቡ በጦርነቱ ምክንያት ከውድድር ርቆ ከቆየ በኋላ በአሰልጣኝ ሀፍቶም ኪሮስ እየተመራ የክልሉ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባዘጋጀው ውድድር ሲወዳደር መቆየቱ ሲታወስ አሁን ደግሞ ቀናት ከፈጀ ውይይት በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ለመቅጠር ተስማምቷል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ መከላከያ፣ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር ማሰልጠን የቻሉት አሰልጣኙ ከአንድ ዓመት በፊት በፋሲል ከነማ ካደረጉት የስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሰው ቢጫዎቹን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።