​ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ14ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የሰበታ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ፍልሚያ እንዲህ ተቃኝቷል።

በብቸኝነት እስካሁን በሊጉ አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ሰበታ ከተማ ከገባበት የውጤት ማጣት ቀውስ ለማገገም እና ከሚገኝበት የደረጃው ቅርቃር መሻሻል ለማስመዝገብ ለመንደርደር ነገ እጅግ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይታሰባል።

ባሳለፍነው ሳምንት የብዙዎች መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ ሰበታ ከተማ ከዋና አሠልጣኙ ዘላለም ሽፈራው ጋር የገባበት ሰጣ ገባ ነው። ድረ-ገፃችን ጉዳዩን በተመለከተ በሰራችው ተከታታይ ዘገባ አሠልጣኙ ተከታታይ የተመዘገቡትን አሉታዊ ውጤቶች በመንተራስ ሰበታ ድረስ መጥተው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ከክለቡ በጊዜያዊ ገለል እንዲሉ ተደርጎ ለሳምንታት ታግደው የነበሩት የቀድሞ ምክትል አሠልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ ወደ ስብስቡ እንዲመጡ ተደርጓል። ያለፉትን ቀናት ቡድኑን ልምምድ ሲያሰሩ የሰነበቱት አሠልጣኝ ብርሃኑም ነገ በጊዜያዊነት ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተመላክቷል። በሜዳም ሆነ ከሜዳም ውጪ ክፉኛ የታመመ የሚመስለው ቡድኑም ጊዜያዊ የአሠልጣኝ ለውጥ ማረጉ ነገ አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣለት ለመናገር ቢከብድም በበርካታ ክለቦች የአሠልጣኝ ለውጥ የሚያመጣው የተነሳሽነት ስሜት ምናልባት ሰበታም ቤት ከተከሰተ ለባህር ዳሮች ፈተና ነው። 

በ8ኛ ሳምነት ጅማን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በአንፃራዊነት መጠነኛ የእንቅስቃሴ መሻሻል እያሳዩ የመጡት ሰበታዎች በዋናነት በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንካራ አለመሆናቸው በየጨዋታዎቹ እጅ እንዲሰጡ ሲያስገድዳቸው ይታያል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎችም በድምሩ 62 የግብ ሙከራዎችን ያደረገ ሲሆን 21ዱን ዒላማውን የጠበቀ አድርጎ ከመረብ ያገናኘው አምስቱን ብቻ ነው። እንደማናፀሪያ ከስድስቱ ጨዋታዎች በፊት በአንድ በላቀ የቀደሙ ሰባት ጨዋታዎች ቡድኑ በድምሩ 42 ሙከራዎችን ብቻ ነበር ያደረገው። ይህ ምን ያህል ወደፊት እየተጠጋ ሙከራዎችን ለማድረግ እየደፈረ እንደሆነ ቢያሳይም ግን የሙከራዎቹ ጥራት የወረደ እንደሆነ በሚገባ መናገር ይቻላል። ጎል ፊት ብቻ ሳይሆን በራሱ ግብ ክልልም ቡድኑ አይበገሬ መሆን ይገባዋል። የሊጉ ብዙ ግብ ያስተናገደው ስብስብም በቶሎ ከደረጃ ግርጌው መሻሻል ለማምጣት ጊዜ ሳይነጉድ በቶሎ መንቃት አለበት። በነገው ጨዋታ ደግሞ ከባህር ዳር ከፍተኛ ፍልሚያ እንደሚጠብቃቸው ቢገመትም ኳስን ለተጋጣሚ ሰጥተው በመልሶ ማጥቃት እንደሚጫወቱ ይታሰባል።

ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት ባህር ዳር ከተማዎች በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ቦታን ከያዘው ሰበታ ከተማ አዎንታዊ ውጤት ለማምጣት እና ከበላያቸው ከሚገኙት ክለቦች ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበበ ብርቱ ትግል ማድረጋቸው የማይቀር ነው።

የውድድር ዓመቱ ጅማሮ ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን ብዙዎች የገመቱት ባህር ዳር ከተማ ገና በ13ኛ ሳምንታት ጨዋታዎች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘጠኝ ነጥቦች ተበልጠው 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በወጥነት ወጥ ያልሆነ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ክለቡም አምስት ጨዋታ አሸንፎ በተቃራኒው አምስት ተሸንፎ ቀሪዎቹን አቻ ወጥቷል። ቡድኑም ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በላይ ድል አድርጎ አለማወቁ ምነኛ በወጥነት እየተጫወተ እንደሆነ የሚያሳይ ጉዳይ ነው። የሆነው ሆኖ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች የድል አልባ ጉዞ በኋላ በሀዋሳ ከተማ ላይ ሦስት ነጥብ የተቀዳጀው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር እጅግ የወረደ እንቅስቃሴ በማድረግ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታውም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጫና በርክቶባቸው ያመሹ ሲሆን አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አለማድረጋቸው ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ወሳኝ ተጫዋቾችን በጉዳት ማጣታቸው መጠነኛ መሳሳት እንዳስከተለባቸው ቢታመንም በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ተጋጣሚ ነገ ስለሚጠብቃቸው ወደ አሸናፊነት ሊመለሱ ይችላሉ።

እንደገለፅነው የወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት የበዛበት ክለቡ ከምንም በላይ በርካታ የመስመር ተጫዋቾቹን ማጣቱ የማጥቃት ሀሳቡ መሐል ለመሐል ብቻ እና ተገማች እንዲሆን ያደረገው ይመስላል። በዋናነት ደግሞ በአጥቂ አማካዩ ፍፁም ዓለሙ ፍጥነት ላይ የተመረኮዘው እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ አደገኛ ቢሆንም ተጫዋቹን ምቾት የማይሰጡ የሰው ለሰው አያያዝ እና የቦታ ንፍጊያ ስልት በሰበታ በኩል ከተዘየደ ቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭ እንደሚያጣ ይገመታል። ከዚህም በተጨማሪ ዋነኛ የሳጥን ውስጥ አጥቂው ኦሴ ማውሊ ጉዳት ላይ መገኘቱን ተከትሎ አሠልጣኝ አብርሃም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች አብዱልከሪም ኒኪማን እንደ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ተጠቅመው በአንዱ ፍሬያማ ሲሆኑ በአንዱ ደግሞ ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህ አጨዋወት ነገም እንደሚቀጥል ሲገመት የተጋጣሚን የኋላ መስመር ለማስከፈት ግን የመስመር ላይ ሩጫዎችም ያስፈልጋሉ።

በሰበታ ከተማ ቡድን መሀመድ አበራ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ እንደማይኖሩ ሲገለፅ አስቻለው ታደሠ እንዲሁም አክሊሉ ዋለልኝ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ አገግመዋል። በባህር ዳር ከተማ በኩል ደግሞ ኦሴ ማውሊ እና መሳይ አገኘው አሁንም ከጉዳታቸው ያላገገሙ በመሆኑ እንዲሁም ግርማ ዲሳሳ እና አህመድ ረሺድ በቅጣት ምክንያት ነገ አይሰለፉም። ከድሬዳዋው ጨዋታ በፊት የተጎዳው ፈቱዲን ጀማል ግን በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

ጨዋታውን ተከተል ተሾመ በዋና ሸዋንግዛው ተባበል እና አበራ አብርደው በረዳት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን እንደሚመሩ ታውቋል።


እርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2012 ያደረጉት ጨዋታ በኮቪድ ምክንያት በመሰረዙ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በሁለት ጨዋታ (ዐምና) የተገደበ ነው። በዚህም በመጀመርያው ዙር ባህር ዳር 4-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር ሰበታ ከተማ 2-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል –  አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ሀምዛ አብዱልሀሚን

ሳሙኤል ሳሊሶ -አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ – ፍፁም ገብረማሪያም 

ዘካሪያስ ፍቅሬ


ባህር ዳር ከተማ (3-4-2-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መናፍ ዐወል – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ 

ሳለአምላክ ተገኘ – አለልኝ አዘነ – በረከት ጥጋቡ – ተመስገን ደረሰ

ዓሊ ሱለይማን – ፍፁም ዓለሙ

አብዱልከሪም ኒኪማ