መልስ ያላገኘው ጥያቄ…

ደመወዝ ሳይከፈላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲያመሩ የተገደዱት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች……

የ2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እሁድ ሐምሌ 7 በንግድ ባንክ አሸናፊነት መጠናናቁ ይታወሳል። ባንኮቹ በተከታታይ ለአራተኛ በአጠቃላይ ለሰባተኛ ጊዜ ዋንጫውን በተቀዳጁበት የውድድር ዘመን በርካታ ተጫዋቾች በደመወዝ አለመከፈል ምክንያት ብዙ ወራትን በጭንቀት እና በሰቀቀን እንዲያሳልፉ ተገድደዋል።


ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንዳስነበብናችሁ እስከ ስምንት ወር የሚደርስ ደመወዝ ባለመቀበላቸው ከምግብ መከልከል ጀምሮ እንደ ንጽሕና መጠበቂያ ያሉ ለሴቶች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት መቸገራቸው የሚታወሱት እና ውድድሩ ካለቀ በኋላ ወደ ቤተሰብ የሚመለሱበት መንገድ ሲያስጨንቃቸው የነበሩት ተጫዋቾቹ የፈሩት ደርሶ የምግብ እና የአልጋ ካልተከፈለ አትወጡም እስከመባል ደርሰዋል።


በደመወዝ ጥያቄዎች ምክንያት በወንዶቹ እጅግ አስከፊ ዓመት ያሳለፈው የሀምበርቾ ቡድን ለሴቶቹ መከፈል ከሚገባቸው የስምንት ወር ደመወዝ ውስጥ የአንድ ወር ደመወዝ ወደ ቤተሰብ መመለሻ መስጠቱ የታወቀ ሲሆን ተጫዋቾቹ ከሦስት ቀናት “ከሆቴል አትወጡም” ቅጣት በኋላ ዛሬ ወደየቤተሰቦቻቸው መንገድ መጀመራቸው ሲታወቅ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ግን አሁንም አዳማ በሚገኘው ያረፉበት ሆቴል እንደቀሩ ተሰምቷል።


በአንጻሩ የይርጋጨፌ ቡና ተጫዋቾች የስምንት ወር ፣ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች እስከ አምስት ወር የሚደርስ ደመወዝ ሳይከፈላቸው መልስ ባለማግኘታቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ መገደዳቸው የተሰማ ሲሆን ሌሎች በርካታ ቡድኖችም እስከ ሁለት ወር ደመወዝ ለተጫዋቾቻቸው መክፈል እንዳልቻሉ ማረጋገጥ ችለናል።

* ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በዲሲፕሊን ኮሚቴው በኩል የሚወስነው ውሳኔ ይጠበቃል።