የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 2ኛ ዙር ጅማሮ ሲጠቃለል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር ትናንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ነጌሌ አርሲ ወደ መሪነት የተሸጋገረበት፣ ኤሌክትሪክ እና ቡራዩ የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱበት እንዲሁም ነቀምቴ በአሸናፊነቱ የቀጠለበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ምድብ ሀ

ወደ ባህር ዳር ያመራው የምድብ ሀ ውድድር በአፄ ቴዎድሮስ ስታደየም የሚካሄድ ሲሆን ትኩረት የሳቡ ውጤቶች እና ክስተቶች ተስተናግደውበታል። ቅዳሜ በ4:00 ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ነጌሌ አርሲ አምቦ ከተማን ገጥሞ 4-1 በማሸነፍ ወደ መሪነት ከፍ ብሏል። የአምቦ ከተማ እጅጉን ዘግይቶ ወደ ስፍራው በማምራቱ የጨዋታው ቀን ባህርዳር በመድረስ ከድካም ሳያገግም ወደ ሜዳ መግባቱ የሳምንቱ ትኩረት ሳቢ ክስተት ሆኗል። ነጌሌ አርሲ በ7ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አምቦ ከተማ የአቻነቱን ግብ አስቆጥረው ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ጉሬሳ ገመቹ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ አርሲ በድጋሚ ቀዳሚ ማድረግ ሲቸል ብሩክ ንፁአምላክ በ70ኛ እንዲሁም ሰይፉ ተካልኝ በ85ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 4-1 አሸንፏል። በጨዋታው አምቦዎች የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ድሉን ተከትሎ ነጌሌ አርሲ ነጥቡን ወደ 23 ከፍ በማድረግ መሪነቱን ከኤሌክትሪክ መረከብ ችሏል።

ቅዳሜ በ8:00 የተደረገው የጋሞ ጨንቻ እና የገላን ከተማ ጨዋታ በገላን አሸናፊነት ተጠናቋል። በ12ኛው ደቂቃ ላይ የኋላሸት ፍቃዱ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብም ገላንን ደረጃውን እንዲያሻሽል ያደረገ ድል እንዲያስመዘግቡ ረድታለች።

በ10:00 የቀድሞ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል። በርካታ የማስጠነቀቂያ ካርድ ያስመልከተው ጨዋታ ከፍተና ፉክክር አስተናግዶ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ሳሙኤል ወንድሙ ባንክን ቀዳሚ ሲያደርግ ኢብራሂም ከድር ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ቢችልም የኋላሸት ሰለሞን ባንክን አሸናፊ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል። በጨዋታው ግብ አስቆጥሮ የነበረው ሳሙኤል ወንድሙ በመገባደጃው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ውጤቱ ለኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ሲሆን ለንግድ ባንክ ደረጃውን ወደ ሦስተኛ ከፍ እንዲያደርግ ረድቶታል።

ዛሬ 8፡00 ላይ ዲላ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሀላባ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተከላካዩ አዩብ በቀታ የበርበሬዎቹን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ባቱ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ፈፅመዋል።

ምድብ ለ

በባቱ ሼር ሜዳ የሚደረገው የምድብ ለ ውድድር የዚህ ሳምንት አመዛኝ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 4:00 ላይ ከንባታ ሺንሺቾን ከ ለገጣፎ ለገዳዲ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በ8:00 የተደረገው የስልጤ ወራቤ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ጨዋታ በኮልፌ 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል። በ20ኛው ደቂቃ ሰለሞን ስንታየው የኮልፌን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።

በ10:00 ሰንደፋ ቤኪ ከ ቡታጅራ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የሰንዳፋ በኬ አጥቂ የነበረው ታምሩ ባልቻን በማሰብ የህሊና ፀሎት ተደርጓል። ጨዋታዎም ምንም ግብ ሳያስመልክተን ተጠናቋል።

የምድቡ ጨዋታ ዛሬ ቀጥሉ ውሎ የምድቡ መሪ ቡራዩ ከተማ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሽንፈት በቤንጂ ማጂ ቡና አስተናግዷል። በቤንች ማጂ 1-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ብቸኛውን የድል ግብ ለአቦሎቹ ያስቆጠረው ሰዒድ ሰጠኝ በ50ኛው ደቂቃ ነው። ውጤቱን ተከትሎ ቡራዩ ከተማ ከለገጣፎ ጋር ያለውን ልዩነት ማስፋት የሚችልበትን እድል ሲያመክን በቅርቡ የቤንች ማጂ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው መሐመድ ኑር ንማ ሥራውን በድል ጀምሯል።

10፡00 ላይ የተደረገው የቂርቆስ ክ/ከተማ እና የካፋ ቡና የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ምድብ ሐ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረገው የዚህ ምድብ ውድድር መክፈቻ መሪዎቹ አሁንም በድል የቀጠሉበት ውጤት ተመዝገቧል። 4:00 ላይ የጅማ አባ ቡና እና የፌዴራል ፖሊስ ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በጨዋታው ፌዴራል ፖሊሶች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በ8:00 አቃቂ ቃሊቲን ከሀምበሪቾ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በ29ኛው ደቂቃ በበድሉ መርዕድ ባስቆጠረው ግብ አቃቂዎች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ቢመሩም ከእረፍት መልስ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ልዑልሰገድ አስፋው በአዲሱ አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ወደ ሜዳ ለገባው ሀምበሪቾ አስቆጥሯል።

በ10:00 ወላይታ ሶዶ እና ኢትዮጵያ መድን ያደረጉት ጨዋታ በመድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለኢትዮጵያ መድን በ46 ኛው ደቂቃ ቻላቸው መንበሩ እና የጨዋታው መጠነቃቂያ ላይ ያሬድ ደርዛ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። በዚህም ነቀምቴ ጨዋታውን ዛሬ እስኪያደርግ ድረስ ነጥቡን ማስተካከል ችሎ ነበር።

ዛሬ 8፡00 ላይ ሌላው የምድቡ መሪ ነቀምቴ ከተማ ደቡብ ፖሊስን 2-0 በማሸነፍ የደረጃ ሠንጠረዡ አናት ከመድን ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት በመመለስ እንዲቀጥል አስችሏል። የነቀምቴን ሁለቱንም ጎሎች አጥቂው ኢብሳ በፍቃዱ ሲያስቆጥር ደቡብ ፖሊሶች በመጨረሻ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ አዲስ አዳጊው ጉለሌ ክፍለ ከተማን ከየካ ክፍለ ከተማ አገናኝቶ ጉለሌ ክ/ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።