ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ14ኛው ሳምንት ትኩረት ከሚስቡ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ጨዋታ እንዲህ ቃኝተነዋል።

የሁለቱ ተጋጣሚዎችን የቅርብ ጨዋታ ውጤቶች እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መዳከም ለተመለከተ ለነገው ጨዋታው የሚገባውን ግምት ላይሰጥ ቢችል አያስገርምም። ሆኖም አምና ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩ መሆኑ እና ዘንድሮም የተሰጣቸው ግምት የነገ ምሽቱን ፍልሚያ ትኩረት እንዲስብ ያደርጋል። ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና እጅግ ደካማ በሆነ አቋም በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈትን አስተናግዶ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተንሸራቶ ይገኛል። በሀዋሳ ከተማ 2-1 የተረታው ፋሲል ከነማም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ልዩነት አምስት ደርሷል። ነገር ግን በተጠባቂ ጨዋታዎች ላይ የሚገኙ ድሎች የቡድኖችን ደካማ አካሄድ የማቃናት ዕድልን ይዘው የሚመጡ በመሆኑ በ13ኛው ሳምንት ሽንፈት ካገጠማቸው ቡና እና ፋሲል ማን አሸናፊ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ከወዲሁ ይጠበቃል።

በተጋጣሚዎቹ ዘንድ የጋራ ድክመት የሆነው የሜዳ ላይ ተነሳሽነታቸው እንደቀደመው ጊዜ ያለመሆኑ ጉዳይ የነገውን ጨዋታ የመወሰን አቅም ካላቸው ነጥቦች ዋነኛው ነው። ከኳስ ውጪ ባሉ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ የቡድንን ቅርፅ በቶሎ ለመያዝ አልያም ከተጋጣሚ ኳስን በፍጥነት ማስጣል የሁለቱ ቡድኖች ፍካጎት ሆኖ ቢታይም በግለሰብ እና እንደቡድን ታጋትን በሚጠይቁት መሰል ቅፅበቶች ላይ ስኬትን የሚያመጣ መነቃቃት ላይ መገኘት ነገ እጅግ አድርጎ አስፈላጊያቸው ይሆናል። ያሉበት የውጤት መንሸራተት ተፈላጊውን መነሳሳት ሊወልድ ቢችልም ምንኛቸው የተሻለ አተገባበር ይኖራቸዋል የሚለው የበላይነታቸው ላይ ተፅዕኖ ይኖራዋል።

በተክቲካዊ ጉዳዮችም ሁለቱም ተመሳሳይ ድክመቶች ይታዩባቸዋል። በተለይም የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው ለማጥቃት ሲሞክሩ ከኋላ የሚተዉት ክፍተት በተደጋጋሚ ሲያስጠቃቸው ይታያል። የፋሲል ከነማ ተከላካዮች ግለሰባዊ ብቃት እና ፍጥነት መውረድ ቡድኑን ቀጥተኛ ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ምን ያህል እንደጎዱት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታዎች ምስክሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ቡናም በጫና የሚያጠቁ ቡድኖች ሲገጥሙት እና የኳስ ፍሰቱ መሀል ላይ ሲቋረጥ በቀላሉ ተጋልጦ ፈተና ውስጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማን ሁለተኛ አጋማሽ ብልጫ ማንሳት ብቻ በቂ ነው። በሁለቱም በኩል ይህንን ደካማ ጎን በተገቢው ቅፅበት ለማግኘት ግን ከላይ የተጠቀሰው የኳስ ውጪ ትጋት ለተጋጣሚዎቹ አስፈላጊያቸው ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡና እንደአርባምንጭ ሁሉ በፋሲልም ከሜዳው በቅብብሎች እንዳይወጣ ከፍ ያለ ጫና ሊገጥመው ቢችልም ከአጫጭር ቅብብሎች ውጪ መካከለኛ አልፎ አልፎ ደግሞ ረዘም ያሉ ኳሶችን በስኬት ወደ ፊት ለማድረስ ምቹ የሆኑት አማካዮቹ ፋሲሎች ከሚያጧቸው ኳሶች የመከላከል ሽግግር ላይ ባሉበት ቅፅበት አደገኛ ኳሶችን በማድረሱ በኩል ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ። እነዚህ ቅፅበቶች ከተፈጠሩ እና ከፊት በጥሩ አጨራረስ ከታገዙ ቡናዎች ግብ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። በፋሲል በኩል ሀዋሳ ከተማ የቅርፅ ለውጥ በማድረግ በኮሪደሮች በኩል የቁጥር ብልጫን ፈጥሮ የደፈነውን ክፍተት ነገ የማግኘት ዕድሉ ሊኖረው ይችላል። በሁለቱም መስመሮች የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን የመስመር ተከላካዮች የሚጠቀመው ቡና ለፋሲል ከነማ የመስመር አጥቂዎች የመንቀሳቀሻ ክፍተት ከተወ እንደበረከት ደስታ ያሉ ተጫዋቾች በቀላሉ አጋጣሚውን ጥቅም ላይ ሊያውሉት እንደሚችሉ ይታመናል።

በአርባምንጩ ጨዋታ ከበድ ያለ ጉዳት ከገጠመው ዊሊያም ሰለሞን ውጪ ኢትዮጵያ ቡና ቀሪው ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ሰዒድ ሁሴን ፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና ሳሙኤል ዮሐንስ በጉዳት ሳቢያ የነገው ጨዋታ እንደሚያልፋቸው ስናረጋግጥ በድኑን ዳግም የተቀላቀለው ሙጂብ ቃሲም በነገው ጨዋታ አጠቃላይ ስብስብ ውስጥ ሊገኝ እንደሚችልም ሰምተናል።

ይህንን ጨዋታ አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት ሱመሩት ክንዴ ሙሴ እና ወጋየሁ አየለ ረዳት ሊዲያ ታፈሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ስምንት ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አድርገዋል። በውጤቱ ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቡና 10 ፣ ፋሲል 7 ግቦችን ማስመዝገብም ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – ሥዩም ተስፋዬ

ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ሮቤል ተክለሚካኤል

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ያጋሩ