ሲዳማ ቡና የተከላካዩን ውል አራዝሟል

ደስታ ደሙ ውሉን አራዝሟል

ቀደም ብለው ሳሙኤል ሳሊሶን እና አበባየሁ ሀጂሶን የግላቸውን ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች የደስታ ደሙን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አራዝመዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ወደ ሲዳማ ቡና ተዘዋውሮ ቡድኑ በሊጉ እንዲተርፍ የራሱን አስተዋጾኦ ያበረከተው ተከላካዩ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመትም በተመሳሳይ በተሰለፈባቸው ሀያ አምስት ጨዋታዎች ቡድኑን በወጥነት አገልግሏል።

በ2005 በአዳማ በተደረገ የታዳጊዎች ውድድር ጥሩ ብቃት በማሳየት በሙገር ሲሚንቶ መልማዮች ዓይን ውስጥ የገባው ይህ ተጫዋች እስከ 2008 ድረስ አሳዳጊ ክለቡን በታዳጊ እና በዋናው ቡድን ደረጃ ካለገለገለ በኋላ በደደቢት ሁለት የውድድር ዓመታት፤ በወልዋሎ አንድ ዓመት እንዲሁም የሊጉን ዋንጫ ባነሳበት ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት የውድድር ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ላለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሲዳማ ቡና ቆይታ ማድረጉ ሲታወስ አሁን ደግማ ከክለቡ ጋር ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለመቆየት ተስማምቷል። ተጫዋቹ ከ20 ዓመት በታች፤ በኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሩን ማገልገሉም ይታወሳል።