ኢትዮጵያ ቡና የክረምቱ አራተኛ ፈራሚውን አግኝቷል

በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ የነበረው ጋናዊ ተጫዋች ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀለ።

በትናንትናው ዕለት የሦስት ተጫዋቾች ዝውውር ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ደግሞ የ21 ዓመቱ ጋናዊ ግብ ጠባቂ ኢብራሂም ዳንላድ ለማስፈረም መስማማታቸው ይፋ አድርገዋል። ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ከአሳዳጊ ክለቡ አሻንቲ ኮቶኮ ጋር የተለያየው ይህ ግብ ጠባቂ ከሌሎች የጋና ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቢቆይም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተስማምቶ በቀጣይ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ክለቡ አስታውቋል።

ተጫዋቹ ባለፈው የውድድር ዘመን በአስራ ሦስት ጨዋታዎችን ቡድኑን ያገለገለ ሲሆን ለሀገሩ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ጨምሮ በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ቡድኖች ጋናን በመወከል ተሳትፏል። ተጫዋቹ በኳታር የ2022 የአለም ዋንጫን ጨምሮ በ2017 ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ዓለም ዋንጫም መሳተፍ ችሏል።