​የአሠልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-1 ባህር ዳር ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከደቂቃዎች በፊት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ብርሃን ደበሌ – ሰበታ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ)

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው ጥሩ ነበር። እንደምንፈልገው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተን ነበር። በዚህም ጥሩ ውጤት አምጥተን እረፍት ወጥተን ነበር። ይሄንንም በሁለተኛው አጋማሽ ለማስቀጠል ሞክረን ነበር። ግን እንዳያችሁት ግብ ገብቶብን ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቀናል። በአጠቃላይ ግን ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ጨዋታውን የቀረቡበት መንገድ ቀጣይነት ይኖረው ይሆን?

ተለዋዋጭ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ተጫዋቾች አቅምም ልንቀያይር እንችላለን። ዱሬሳ ግን ከመስመር የሚነሳ ስለሆነ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ነው የሚያደርገው። ይሄንንም አጠናክረን እንቀጥላለን። ለወደፊቱም ከዚህም የተሻለ ነገር ለመስራት እንሞክራለን። 

በውጤቱ ደስተኛ ነህ?

ውጤቱ ምንም አይልም። በመካከለኛ ደረጃ ነው። ከቅርቃሩ ለመውጣት ማሸነፍ ነበረብን። ሦስት ነጥብ ያስፈልገን ነበር። አቻም ግን ምንም አይደለም። 

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው ክፍተት?

ያገኘነውን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ወደ ኋላ ትንሽ አፈግፍገን ነበር። ይህ ነው ትንሽ ያዝ ያደረገን።

አብርሃም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ጥሩ ነበር ማለት እችላለሁ። ሙሉውን ጨዋታ ተቆጣጥረን ወጥተናል ብዬም አስባለው። ነገርግን በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካዮቻችን የመግባባት ስህተት እና የጥንቃቄ ጉድለት የገባብን ኳስ ዋጋ አስከፍሎናል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ግን ሙሉውን የጨዋታ ብልጫ ይዘን ተጫውተናል። ለማግባት ከነበረን ፍላጎት እና ጉጉት ውጤቱን ወደማሸነፍ መቀየር ባንችልም አንድ ለአንድ መውጣታችን በቂ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለተጋጣሚያቸው ሰበታ አቀራረብ?

ጥሩ ነው የተጫወቱት። ከሽንፈት መውጣት ስለፈለጉ ወደኋላ በዛ ብለው ነበር የተጫወቱት። እኛም በሁለተኛው አጋማሽ የአጥቂውን ክፍል ወደፊት በመጨመር ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረናል። ግን  ወደ ግብ መቀየሩ ላይ በነበረብን ድክመት አቻ ልንወጣ ችለናል። በተረፈ ግን የሰበታ ቡድን ካለፉት ጨዋታዎች የተሻለ በሚባል ሁኔታ ቅርፅ ያለው እንቅስቃሴ አድርጓል።

                                                 

ያጋሩ