የኬኒያ ፖሊስ አቋሙን ሊፈትሽ ነው

የኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሲያመቻች የመጀመርያውን ዙር ጨዋታ በሜዳው ለማስተናገድም በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል።

በመጀመርያው ዙር የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥመው ኬኒያ ፖሊስ ለማጣርያው ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ከዩጋንዳው ቫይፐርስ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርግ ነው። ከቀናት በፊት የወንዶች ቡድኑ ‘የሞዛርት ቤት’ ዋንጫ፤ የሴቶች ቡድኑ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው ተከትሎ በናይሮቢ ኦሌ ሴሬኒ ሆቴል በተዘጋጀው የእውቅና ስነስርዓት ላይ ክለቡን በበላይነት የሚያስተዳድረው የሀገሪቱ የፖሊስ ተቋም ለቡድኑ ከወዲሁ ከፍተኛ በጀት መመደቡን ገልፆ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ አንድ አካል የሆነ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርግም ገልጿል።

በእውቅና እና የዋንጫ ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሀገሪቱ ውስጥ ደኅንነት እና ብሔራዊ አስተዳደር ዲፓርትመንት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ሬይመንድ ኦሞሎ ተቋሙ ለቡድኑ 19 ሚሊዮን የኬኒያ ሽልንግ መመደቡን ገልጸው ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በፊት ከዩጋንዳው ቫይፐርስ ጋር እንደሚጫወቱም አረጋግጠዋል።

በኡሊንዚ ስፖርት ኮምፕሌክስ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ በመደበኛ እና በጭማሪ ሰዓት ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ተጋጣሚውን KCb በመለያ ምቶች ያሸነፈው የኬንያ ፖሊስ በታሪኩ የመጀመርያ በሆነው አህጉራዊ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ለመግጠም በዝግጅት ላይ ይገኛል። በተያያዘ ዜና በኬኒያ የሚገኙ ስታዲየሞች ካፍ ያስቀመጠውን የጥራት ደረጃ ባለማሟላታቸው የመጀመርያውን ዙር ጨዋታ ከሀገራቸው ውጭ እንደሚያከናውኑ ሲገለፅ ቢቆይም የካፍ ልኡካን ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኘው የንያዩ ስታዲየምን ፍቃድ ለመስጠት በጥሩ ሂደት ላይ እንዳለ የሀገሪቱ የወጣቶች፣ ስነ-ጥበባት እና ስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ ፒተር ቱም ተናግረዋል።