[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጨዋታቸውን በአንድ አቻ ውጤት ፈፅመዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በአርባምንጭ ከተማ ከተረታው ስብስብ ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ቴዎድሮስ በቀለ፣ ሥዩም ተስፋዬ እና ዊሊያም ሰለሞንን አስወጥተው በምትካቸው የመጀመሪያ ጨዋታውን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ያደረገው ገዛኸኝ ደሳለኝ እንዲሁም ሚኪያስ መኮንን እና ሮቤል ተክለሚካኤልን በመተካት ሲያስገቡ በተመሳሳይ ፋሲሎች በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፈው የመጀመሪያ ተመራጮች ውስጥ በተመሳሳይ ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን አስቻለው ታመነ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ኦኪኪ አፎላቢን አስወጥተው በምትካቸው አምሳሉ ጥላሁን፣ በዛብህ መለዮ እና ፍቃዱ ዓለሙን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።
ሁለቱን ቡድኖች ከሽንፈት መልስ እንደመገናኘታቸው በተሻለ ተነሳሽነት ከጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ይዘው ለመውጣት የተሻለ ጥረት ያደረጉበት ጨዋታ ነበር። በእንቅስቃሴ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች በተለይ ኳሶችን በመቀባበል ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ከነበራቸው ፍላጎት አንፃር በተወሰነ መልኩ መሀል ሜዳው ላይ ጠንከር ያለ ፉክክር ያስተዋልንበት ጨዋታ ነበር።
በ12ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀውን ሙከራ ያስመዘገቡት ፋሲል ከነማዎች ነበሩ። በረከት ደስታ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አጥብቦ በመግባት የሞከረውን ኳስ አቤል ማሞ ሊያድንበት ችሏል።
ከሙከራው ውጭ በአጋማሹ በእንቅስቃሴ ረገድ ፋሲሎች በኢትዮጵያ ቡናዎች ብልጫ የተወሰደባቸው አጋማሽ ነበር። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአርባምንጩ ጨዋታ በተሻለ በቀጥተኛ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ረገድ የተሻለ አጋማሽ ቢያሳልፉም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ሙከራ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በ36ኛው ደቂቃ ፋሲሎች በኢትዮጵያ ቡና የኳስ ምስረታ ሂደት ከአማኑኤል ዮሐንስ እግር የነጠቁትን ኳስ በረከት ደስታ እና በዛብህ መለዮ በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል አልፈው በዛብህ መለዮ በግሩም አጨራረስ ፋሲል ከነማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
በ42ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች የአበበ ጥላሁንን ስህተት ተጠቅመው ሁለተኛ ግባቸውን ለማግኘት ቀርበው የነበረ ቢሆንም የአቤል ማሞ ኳሷን ሲያድን በሰከንዶች ልዩነት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ አቡበከር ናስር ወደ ግብ ልኳት የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው አበበ ጥላሁን በማስቆጠር ቡድኑን በአቻ ውጤት ወደ እረፍት እንዲያመራ አስችሏል።
የሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሁሉ በርከት ያሉ አካላዊ ፍትጊያዎች እና ጥፋቶች ታጅቦ ነበር ጅማሮውን ያደረገው። ፋሲሎች አጋማሹን በተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት በመጀመር በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡናን ሳጥንን መጎብኘት ችለዋል። በተለይም በ59ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ አከታትሎ ያደረጋቸው እና አቤል ማሞ እና የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ሁለቱን የመስመር አጥቂዎቻቸውን በአዲስ ጉልበት በመተካት የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ በተረጋጋ መልኩ ኳሶችን በመቆጣጠር ሆነ ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ፍፁም ተዳክመው ተመልከተናል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ሆነ በቀጥተኛ አጨዋወት ኢትዮጵያ ቡናን መፈተናቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በተለይም በ82ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና አቤል ያዳነበት አስደናቂ ሙከራ ሌላ በአጋማሹ የተመለከትነው የግብ ማግባት ሙከራ ነበር።
ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በአንድ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 23 በማሳደግ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ19 ነጥብ ባሉበት 7ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።