[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ያለፉትን ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፉት ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ተዳሷል።
በመቀመጫ ከተማው ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ድሬዳዋ በወጥነት ውጤቱን ለማሻሻል እና ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ራሱን ፈቀቅ ለማድረግ ነገ ሦስት ነጥብን እያሰላሰለ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። በተቃራኒው የአቻ ውጤቶችን ያበረከተው አዳማ ከተማም በተመሳሳይ ወደ ወጥ ብቃት ለመምጣት እና በውድድር ዓመቱ ያሸነፋቸውን ጨዋታዎች ቁጥር አራት ለማድረስ ድልን ተቀዳሚ ዕቅዱ አድርጎ ጨዋታውን እንደሚጀምር ይታመናል።
ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በጊዜያዊ አሠልጣኙ ፎዐድ የሱፍ እየተመራ አንዱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ ሁለቱን አቻ የወጣው ድሬዳዋ በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል ሲያሳይ አስተውለናል። በኳስ ቁጥጥር ወቅት ቀጥተኝነት የሚጎለው ቡድኑም ባሳለፍነው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ቢለያይም የኳስ ቅብብሎቹ ፍጥነት የተሞላባቸው እና የፊትዮሽ ሆነው ነበር። በዋናነት ደግሞ ቁመታሙ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መሐከል ያገኘ ይመስላል። በባህር ዳሩም ጨዋታ ቡድኑ ዘንድሮ ካደረጋቸው ሙከራዎች የበለጠውን (13) አከናውኖ መውጣቱ ምንኛ ወደተጋጣሚ ሳጥን እየተጠጋ እንደመጣ ያሳያል። እንዳልነው ደግሞ ሙኸዲን እንደ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ተጫውቶ ባክኖ ከሚወጣባቸው ጨዋታዎች በኋላ የሲዲቤ መግባት በሳጥን ውስጥ ሞገስ እንዲመጣ እንዳደረገው መናገር ይቻላል። ተጫዋቹ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እና የተከላካዮችን ትኩረት ስቦ አጋሮቹ ክፍት ሜዳ እንዲያገኙ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ጀርባውን ለጎሉ ሰጥቶ በአንድ ሁለት ቅብብል የሚጫወትበት መንገድም ለተከላካዮች ከባድ ነው። ነገም ብርቱካናማዎቹ በዚሁ የጨዋታ ሂደት እንደሚቀርቡ ሲገመት ለአዳማ የኋላ መስመርም ፈተና እንደሚሰጡ ይታመናል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከሲዳማ ቡና ጋር በጣምራ በሊጉ ትንሽ ጨዋታዎችን የተሸነፈው አዳማ ከተማ በበኩሉ በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶችን አስመዘገበ እንጂ አሁን ካለበት ከሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ አካፋይ ተስፈንጥቶ መሪዎቹ ተርታ በተገኘ ነበር። በተለይ የኋላ መስመሩ ጥንካሬ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በቀላሉ ግቡን እንዳያገኙበት ያደረገ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በመከላከያ ሲረታ ግን መጠነኛ መላላት አጋጥሞት ነበር። እርግጥ የሚሊዮን አለመኖር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ብንረዳም በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ያስተናገዱበት ሂደት ግን ከመዋቅር ባለፈ የግለሰብ ስህተት (የግብ ጠባቂው ጀማል) የተንፀባረቀበት ነበር። ሁለቱም ጎሎች ሲቆጠሩ ደግሞ የመስመር ተሻጋሪ እና የቆመ ኳስን በሚገባ ካለመቆጣጠር የመጡ መሆናቸው ሲታወስ ደግሞ ነገም ድሬዳዋዎች ሊከተሉት ከሚችለው ቀጥተኝነት የተሞላበት አጨዋወት ጋር ተያይዞ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ያሳስባል። በተቃራኒው በተጋጣሚ ሳጥን የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ ያለመጠቀም አልፎም ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ የመፍጠር ችግር ያለበት ቡድኑ ምንም እንኳን ዋነኛ አጥቂው ዳዋ ሁቴሳን ባይጠቀምም ጅማ አባጅፋርን ካሸነፈበት እና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ በርከት ያለ ጊዜ የተጋጣሚን ግብ ለመጎብኘት የተሞከረበት ጨዋታ ነበር ያሳለፈው። ነገ ደግሞ ይህ ሂደት ተጠናክሮ ከቀረበ ዳዋም ቅጣቱን ጨርሶ ስለሚመለስ ለቡድኑ የፊት መስመር ከፍተኛ ብርታት የሚሰጥ ይሆናል።
በነገው ጨዋታ የአማካይ መስመሩ ፍልሚያ ጨዋታውን እንደሚወስን ይገመታል። ከጨዋታ ጨዋታ በመሐል ሜዳው ላይ ጥሩ ብርታት የሚታይበት ድሬዳዋ በተለይ በሁለቱ ዳንኤሎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተቃራኒም ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠትም ሆነ ወደፊት ተጠግቶ ተጋጣሚን በማስጨነቅ የተዋጣላቸው ብቃት የሚያሳዩት አማኑኤል እና ዮሴፍ የሚያደርጉት ፍትጊያ ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚገኙት ፈጣኖቹ የመስመር ተጫዋቾችም ቀጥተኛ የመስመር ላይ ሩጫዎችን በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚደረጉ ሂደቶችም ትኩረትን እንደሚስቡ ይታመናል። በአዳማ ከተማ በኩል ግን የመጀመሪያዎቹ አስር እና አስራ አምስት ደቂቃዎች ላይ የሚታዩት የትኩረት ማነስ ችግሮች ነገም እንዳያገረሹ መደረግ የግድ ይላል። በሜዳቸው የሚጫወቱት ድሬዳዋዎች በቶሎ ውጤት ለማግኘት ሊያደርጉት ከሚችሉት ጫናም መውጫ ሁነኛ ዘዴ መፈለግ ያስፈልጋል። ይህ ቢሆንም ግን ጨዋታዎችን የማሸነፍ መጠነኛ ጫና ያለባቸው ድሬዎች መጠን ካለፈ ፍላጎት ጨዋታውን እንዳያከናውኑ አሠልጣኞቹ ሥራዎችን መከወን ይጠበቅባቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። ጉዳት ላይ የነበሩት ጋዲሳ መብራቴ፣ እንየው ካሳሁን እና ብሩክ ቃልቦሬን ጨምሮ በግል ችግር የተነሳ ለበርካታ ቀናት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው የመሐል ተከላካይ አውዱ ናፊውም ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተመላክቷል። በአዳማም በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት አምስት ቢጫ አይተው የተቀጡት ዳዋ ሁቴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞን ለጨዋታው ብቁ ናቸው ተብሏል።
10 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ከረዳቶቻቸው ፋሲካ የኃላሸት እና ደረጀ አመራ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው እያሱ ፈንቴ ጋር በመሆን ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ 18 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 8 ጨዋታ በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ 6 አሸንፏል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። አዳማ 17 ፣ ድሬዳዋ 15 ጎሎችንም በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሣሁን – አቤል አሰበ – መሳይ ጳውሎስ – ሄኖክ ኢሳይያስ
ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ
ማማዱ ሲዲቤ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ጀሚል ያዕቆብ – ሚሊዮን ሰለሞን – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሁቴሳ – አሜ መሐመድ