ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በነገው የምሽት ጨዋታ ዙሪያ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

13ኛው የጨዋታ ሳምንት ድል ይዞላቸው ከመጡ ቡድኖች መሀል የሆኑት ሀዋሳ እና መከላከያ ተከታታይ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ይገናኛሉ። ከባህር ዳሩ ሽንፈት በቶሎ ያገገመው ሀዋሳ ከተማ ከላይኛው ተፎካካሪዎች አንዱ የሆነውን ፋሲልን መርታት ሲችል ነገ ድል ከቀናው ደግሞ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ይበልጥ ለማጥበብ ዕድል ያገኛል። ገጥሞት ከነበረው የውጤት እጦት ቀስ በቀስ እያገገመ የሚገኘው መከላከያም ነጥቡን 20 በማድረስ ዳግም የሰንጠራዡን አጋማሽ ለማለፍ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ውጤት ማሳካት ያስፈልገዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ መሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን በሜዳም ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥንካሬያቸውን የሚያመላክት ነው። በአብዛኛው ለተጋጣሚ ኳስን ለቆ የሚጫወተው የአሠልጣኝ ዘርዓይ ቡድን በፋሲሉ ጨዋታ ሳይጠበቅ የተጫዋች እና የአደራደር ለውጥ አድርጎ የተጋጣሚን የጨዋታ ሂደት ያመከነበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸረው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በፈጣን ሽግግሮች እና የመልሶ ማጥቃቶችም ተጋጣሚን ለማስደንገጥ ሲጥሩ ታይቷል። በነገው ጨዋታ ግን ከእነርሱ በላይ ኳስን ለመቆጣጠር ፍላጎት የሌለው ቡድን ስለሆነ የሚገጥማቸው የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው በወሳኝ የሜዳ ክፍሎች ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን መወሰን ይጠበቅባቸዋል።

ከውጤት አንፃር ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ የሚሰጠውን ቦታ በማሰብ ጨዋታውን ማድረግ ያለፈ ጉጉት እንዳያመጣ ጥንቃቄ መደረግ ቢገባውም ቡድኑ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ አናት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳመር ከባለፈው ጨዋታ በተለየ የማጥቃት ባህሪ ተላብሶ እንደሚጫወት ይታሰባል። የቡድኑ የልብ ምት የሆኑት ሦስቱ አጥቂዎች (ብሩክ፣ ኤፍሬም እና መስፍን) ፍጥነታቸውን ተጠቅመው ለመከላከያ ተከላካዮች የራስ ምታት እንደሚሆኑ እሙን ነው። በተቃራኒው ደግሞ መከላከያ ከኳስ ውጪ በማሳለፍ የሚሰነዝራቸውን አስደንጋጭ የመልሶ ማጥቃቶች መቆጣጠርም በጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ለማምጣት አስፈላጊ ነው።

ከአዳማው ድል በኋላ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሰጡት አስተያየት ስለቡድናቸው አቀራረብ ብዙ ይናገራል። ጦሩ አሁን ላይ የጨዋታ ውበት ሳይሆን ውጤት አብዝቶ የሚያስፈልገው በመሆኑ በነገውም ጨዋታ አንድ ግብ ማስቆጠር ከቻለ አስጠብቆ ለመውጣት ከፍ ያለ ጥረት ማድረጉ አይቀርም። በእርግጥ የሀዋሳን ቡድን በሚመጥን መልኩ ትኩስ የወጣት ኃይልን በስብስቡ ውስጥ የያዘው መከላከያ በቡድን ቅንጅት ስናስተያየው ግን አብሮ በቆየው ተጋጣሚው ብልጫ ይወሰድበታል። ከዚህም አንፃር ለሀዋሳ የፊት መስመር የመሮጫ ክፍተትን ሳይሰጥ ወደ ራሱ የግብ ክልል በመጠጋት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመድረስ መሞከር ከመከላከያ ይጠበቃል።

በዚህ የማጥቃት ሂደት ውስጥ የቡድኑ ደካማ ጎን ተደርጎ የሚወሰደው በሰሞኑ ጨዋታዎች የግብ ምንጩ የሆነው የቆመ ኳስ ብቻ የመሆኑ ነገር ነው። በእርግጥ ለቀጥተኛው የቡድኑ አጨዋወት ቁልፍ ሚና ያለው ኦኩቱ ኢማኑኤል ወደ ሜዳ ከተመለሰ አንድ ጨዋታ ብቻ መሆኑ ተፅዕኖ ቢኖረውም ሊጉ ሲጀምር ወደነበረው የመጥቃት መዳረሻነቱ ለመመለስ የነገው ጨዋታ መነሻው ሊሆን ይችላል። ቢኒያም በላይ ከመስመር እየገፋ ሰብሮ ለመግባት ከሚጥርባቸው ቅፅበቶች በተጨማሪም የተጨዋቹ መመለስ ለመከላከያ ከክፍት ጨዋታ ግቦችን የማግኛ ሌላ መንገድ እንደሚያስገኝለት ይጠበቃል። ይህም ቢሆን ግን ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች የሚፈጥረው አደጋ ነገም ግብ ይዞለት አይመጣም ማለት አይቻልም።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ሙሉ ስብስባቸውን የመጠቀም ዕድልን ይዘው እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

የምሽቱ ጨዋታ በዮናስ ማርቆስ የመሀል ዳኝነት ሲመራ ሙስጠፋ መኪ እና ዳዊት ገብሬ በረዳትነት አባይነህ ሙላት ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 28 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 12 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መከላከያ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በርካታ በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 60 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 34 ፣ መከላከያ 26 ጎሎችን አስቆጥረዋል። በመጨረሻ 3 ግንኙነታቸው ብቻም 12 ጎሎች ተቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መድሀኔ ብርሀኔ

ወንድማገኝ ኃይሉ – አብዱልባስጥ ከማል – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

መከላከያ (4-4-2)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ

ግሩም ሀጎስ – ኢማኑኤል ላርዬ – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ

ኦኩቱ ኢማኑኤል – ተሾመ በላቸው

ያጋሩ