ቅዱስ ጊዮርጊስ በቲፒ ማዜምቤ በድምር ውጤት 3-2 ተሸንፎ ከቻምፒዮንስ ሊግ ውጪ ሆነ

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ 1ኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ስታደ ቲፒ ማዜምቤ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ቲፒ ማዜምቤ በመጨረሻዎቹ ደቂዎች ባገኛት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ታግዞ 1-0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፈውን ውጤት ማግኘት ችሏል፡፡

ካለ ግብ በተጠናቀቀው የመጀመርያ አጋማሽ ኳስ በመቆጣጠር በኩል የቲፒ ማዜምቤዎች የተሸሉ የነበሩ ቢሆን የተደራጀ የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ሰብረው በመግባት ግብ ማስቆጠርም ሆነ አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ከእረፍት መልስ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥቁር እና ነጭ ለባሾቹ በእንቅስቃሴ ተሸለው ቢገኙም የግብ ሙከራዎቻቸው በሙሉ ኢላማቸውን የሳቱ ነበሩ፡፡ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቲፒ ማዜምቤ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበሃይሉ ፣ ራምኬል እና አዳነ አማካኝነት የቲፒ ማዜምቤው ግብ ጠባቂ ኦሆዶን መፈተን ችለዋል፡፡

በ85ኛው ደቂቃ በአዳማ ትራኦሬ ተቀይሮ የገባው ሶሎሞን አሳንቴ በመጀመርያ የኳስ ንክኪው ኳስ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይዞ ሲገባ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የእለቱ አርቢቴር በአጨቃጫቂ ሁኔታ ለቲፒ ማዜምቤ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምትም ጆናታን ቦሊንጊ ወደግብነት ቀይሮ ቲፒ ማዜምቤ በሜዳው ድል ያደረገበትን ውጤት እንዲያስመዘግብ አድርጓል፡፡ ጨዋታው በጥሩ እንቅስቃሴ ታጅቦ ቢካሄድም አጨራረሱ ግን ውዝግብ አላጣውም፡፡ ለቲፒ ማዜምቤ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢ እንዳልሆነ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተቃውሞ ያቀረቡ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረችው የዲሞክራቲክ ኮንጎ የሬድዮ ጋዜጠኛ የፍፁም ቅጣት ምቱ አጨቃጫቂ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ የዲሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ በድምር ውጤት 3-2 በመርታት ወደ 2ኛው ዙር ሲያልፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ2013 በኋላ ወደ 2ኛ ዙር የመግባት ተስፋውን አጨልሞበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *