ሪፖርት | አዳማ ከተማ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ አግኝቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ድንቅ የሁለተኛ አጋማሽ በነበረው ጨዋታ አዳማ ከተማ በመቀመጫ ከተማው እየተጫወተ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማን በመርታት ከድል ጋር ተገናኝቷል።

ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይተው የዛሬውን ጨዋታ የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጨረሻ ተቀዳሚ አሰላለፋቸው አንድም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ በመከላከያ አንድ ለምንም ከተረቱበት የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ የተጫዋች እና የአደራደር ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በ3-5-2 አደራደር ቅርፅ ከቅጣት የተመለሱት ሚሊዮን ሰለሞን እና ዳዋ ሁቴሳን እንዲሁም ዘካሪያስ ከበደን በአብዲሳ ጀማል፣ አቡበከር ወንድሙ እና ዮናስ ገረመው ምትክ በአሰላለፋቸው አካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታውን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ገና አንድ ደቂቃ ሳይሞላው በ36ኛው ሰከንድ በአሜ መሐመድ አማካኝነት ኳስ እና መረብን አገናኝተው የተሳሳተ የመስመር ዳኝነት ውሳኔ ተከስቶ ጎሉ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሯል። በመቀመጫ ከተማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሰዓት ላይ እየተጫወቱ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ የመዓዘን ምትን መነሻ ካደረገ አጋጣሚ ዳንኤል ኃይሉ ከሳጥን ውጪ በሞከረው ኳስ የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረዋል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋዎች 5 የነበሩትን የአዳማ ተከላካዮች ማስከፈት ተስኗቸው በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጪ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።

ከወትሮው በተለየ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ የጣሩት አዳማዎች በ16ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ከወደቀኝ ካደላ ቦታ የተገኘ የቅጣት ምት ሲሻማ አሜ በግንባሩ ገጭቶት እግሩ ላይ የደረሰው ጀሚል ያቆብ ኳስ እና መረብን አገናኘ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመሐል ተከላካዮቹ አዲሱ ተስፋዬ እና ቶማስ ስምረቱ የፈጠሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ አብዱለጢፍ መሐመድ ኳስ አግኝቶ የጀማልን መረብ ለማግኘት ሞክሮ ወጥቶበታል። በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር የተስተዋለ ሲሆን በ41ኛው ደቂቃ ግን አሜ አዳማን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመራ ነበር። ነገርግን መሳይ ጻውሎስ ተጫዋቹ ላይ ጫና አሳድሮ ኳሱ የግቡን መስመር እንዳያልፍ አድርጓል። አጋማሹም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

በርከት ባሉ ደጋፊዎቻቸው ፊት ጨዋታውን የሚከውኑት ድሬዳዋዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ለማድረግ የአዳማ የግብ ክልል ተገኝተዋል። በ54ኛው ደቂቃም አብዱለጢፍ ከሦስቱ የአዳማ ተከላካዮች የቀኝ ስፍራ ሰፊ የመጫወቻ ቦታ አግኝቶ ከሲዲቤ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ግብ ጠባቂው ጀማል ግቡን አጥቦ በመውጣት ዕድሉ እንዲመክን አድርጎታል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሮ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማዎች ሙሉ ሰዓት ላይ በአምበላቸው አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም ዳዋ ከርቀት የተላከለትን ኳስ ተከላካዮችን አምልጦ በመውጣት የግብ ክልሉን ለቆ ኳሱን ለማምከን የወጣው የግብ ዘቡ ፍሬው አናት ላይ በመላክ ድንቅ ጎል አስቆጥሯል።

ወደመሪነት የተሸጋገሩት የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጫዋቾች ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የተገኘን የመልስ ውርወራ ከተከላካዮች ጀርባ የተረከበው አሜ ፍጥነቱን እና የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የቡድኑን መሪነት አሳድጓል። እጅግ ሳቢ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ75ኛው ደቂቃ ሌላ ጎል አስተናግዷል። በሁለት ጎል ልዩነት የሚመሩት ድሬዎች በቀሪው ደቂቃ በጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት የአዳማው ግብ ጠባቂ ጀማል ረድቷቸው ግብ አግኝተዋል። በዚህም ከመዓዘን ምት የተቀበለውን ኳስ አብዱለጢፍ ገፍቶ በመውጣት ሲያሻማው ጀማል ጣሰው በወረደ የውሳኔ አሰጣጥ ኳሱን መቆጣጠር ተስኖት ሲለቀው ዳንኤል ደምሱ አግኝቶት በአንድ ንክኪ ግብ አድርጎታል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የመልሶ ማጥቃትን እንደ ዋነኛ የግብ ምንጭ በመጠቀም ጨዋታውን ለመግደል ያሰቡ የሚመስሉት አዳማዎች በ82ኛው ቀይረው ወደሜዳ ባስገቡት አቡበከር ወንድሙ አማካኝነት ባገኙት ዕድል ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በ87ኛው ደቂቃም ሌላ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አስመልክተው ወደ ድሬ የግብ ክልል ያመሩት አዳማዎች በዳዋ አማካኝነት አራተኛ ግብ ሊያስቆጥሩ ሲሉ ግብ ጠባቂው ፍሬው ክልሉን ለቆ ኳስ በእጁ በመንካቱ ከጨዋታው በቀይ ካርድ እንዲወጣ ሆኗል። ጨዋታውም ጥሩ ፉክክር አስመልክቶ ፍፃሜውን አግኝቷል።

አዳማ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ቀድሞ በሰበሰበው 16 ነጥብ ያለበት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ቀጥሏል።

ያጋሩ