​የአሠልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-3 አዳማ ከተማ

 [iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ውጤቱ እንዴት ነው?

ስታሸንፍ ደስ ይላል። ስህተቶች ነበሩ። እነሱን ማስተካከል ይጠበቅብናል። ግን በሁሉም መልኩ ጨዋታውን በልጠን ነው የተጫወትነው። ማሸነፋችን ተገቢ ነው ብዬ አስባለው። ብዙ የጎል ዕድሎችም ፈጥረናል። የሳትናቸው የጎል ዕድሎችም አሉ። እነርሱን ማስተካከል ይጠበቅብናል። እንደ ቡድን ግን ሁል ጊዜ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ እንለፋለን። ሜዳ ላይ የተሻልን ብንሆንም ሦስት ነጥብ እያገኘን አልነበረም። ይሄ ሦስት ነጥብ ለእኔም ለተጫዋቾቼም ብዙ ነገር ነው።

ጨዋታውን የቀረቡበት መንገድ?

እነሱ (ድሬዳዋዎች) ተጭነው ወደ ግማሽ ሜዳ ተጠግተው እንደሚጫወቱ ስለምናውቅ የእነሱን ጀርባ ለመጠቀም ሁለት በፍጥነት የሚሮጡ ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል። ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስም በሙሉ ሀይላችን ለማጥቃት ሞክረናል። አሁንም ግን መሐል ሜዳ ላይ የሚቆራረጡ ኳሶች አሉ። እነሱን ማስተካከል ይጠበቅብናል። እንደ ቡድን ግን ሦስት ነጥብ በማግኘታችን ደስ ብሎኛል።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች…?

እግርኳስ አንዳንዴ እንደ ሁኔታው የሚቀያየር ነው። በዚህ መንገድ ላንቀርብ እንችላለን። ግን ሁልጊዜ ኳሶችን ከሜዳችን ጀምረን በፍጥነት ለማጥቃት ነው የምንሞክረው። ይሄ የጨዋታ ዘዴያችንንም ይዘን እንቀጥላለን።

ፉዐድ የሱፍ – ድሬዳዋ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ)

በጨዋታው እቅዳቸውን ተግባራዊ ስለማድረጋቸው?

እቅዳችንን ተግባራዊ አላደረግንም። ይህ የእግርኳስ ክስተት ነው። የጠበቅነውን ነገር አላገኘንም። የኋላ መስመራችንም ጥሩ አልነበረም። በተለይ ከእረፍት በኋላ የነበራቸው አደረጃጀት ጥሩ አልነበረም። ይህ ያለመረጋጋት ሁኔታም ዋጋ አስከፍሎናል። 


እረፍት ሰዓት ክፍተቱን ማስተካከል ስላለመቻሉ?

እረፍት ላይ ተነጋግረን ነበር። ክፍተቶቹን አይተን ያንን ክፍተት እንዲዘጉ አድርገን ነበር። አጋጣሚ ተቆርጠው ገቡ። ዳዋም የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠረ። ግብ ጠባቂያችንም የሰዓት አጠባበቁ ልክ አልነበረም። ያንን ተጠቅመው አገቡብን። ሁለተኛውም ላይ የእኛው ስህተት ነው። እዚህ ላይ በቀጣይ ሰርተን እንመጣለን። 

ውጤቱ አሳማኝ ነው?

አሳማኝ አይደለም። ግን ይህ እግርኳስ ስለሆነ ሽንፈትን ትቀበለዋለህ። ስለዚህ በፀጋ መቀበል ነው። ደጋፊዎቹም ደስተኛ አደሉም። 

ውጤቱ ስለሚያመጣው ጫና?

ምንም ማረግ አንችልም። ይህ እግርኳስ ነው። ባሉት ተጫዋቾች ነው መጠቀም የያዝነው። በመጀመሪያው አሠልጣኝ ተመርጠው በመጡት ተጫዋቾች ነው እየተጫወትን ያለነው። ያለንን እያስተካከልን መሄድ ነው የያዝነው። ቀጣይ ላይ በክፍተታችን ቦታ ላይ ጥሩ ተጫዋቾችን አምጥተን ቡድኑን የተሻለ ቦታ ላይ እናደርጋለን ብዬ አስባለው።

ስለግብ ጠባቂው ፍሬው እንቅስቃሴ…?

የመጀመሪያው ጎል ላይ የእርሱ የሰዓት አጠባበቅ ችግር ነው። ይሄ ትልልቅ ግብ ጠባቂዎች ላይም የሚከሰት ስለሆነ ምንም ማድረግ አንችልም። ቀይ ካርዱም አግባብ አልነበረም። አንደኛ የእርሱ የሰዓት አጠባበቅ ችግር ነበር። ሁለተኛ ደግሞ የእኛ የተከላካይ መስመር በመዘናጋቱ ነው ይሄ የመጣው። ተከላካዮቻችን ከዚህ በፊት በነበረው ሁለት ጨዋታ ጥሩ ነበሩ። ጎልም ሳይቆጠርብን ነበር የወጣነው። ዛሬ ግን ከእረፍት በኋላ የነበረው ነገር ጥሩ አደለም። ለግብ ጠባቂውም ችግር ሊፈጥር የቻለው የእነርሱ አደረጃጀት ጥሩ ባለመሆኑ ነው።