ሪፖርት | በክስተቶች በተሞላው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወደ መሪው የተጠጋበትን ድል አስመዝግቧል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶች ፣ አንድ ቀይ እና 9 ቢጫ ካርድ እንዲሁም አምስት ግቦች በተመዘገቡበት አስገራሚው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን ልዩነት ለጊዜውም ቢሆን ወደ አንድ አጥበዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ፋሲል ከተማን ከረታው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ወንድማገኝ ማዕረግ እና ተባረክ ሂፋሞን አስወጥተው በምትካቸው አዲስዓለም ተስፋዬ እና ብሩክ በየነን ተክተዋል። በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ አዳማን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ኢብራሂም ሁሴንን በገናናው ረጋሳ ብቻ ለውጠው የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

በግቦች የታጀበ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተመጣጣኝ የነበረ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኳስን በመቆጣጠር እና መሀል ለመሀል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጥሩ የነበሩት ሀዋሳዎች በ12ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስን አዲስዓለም ተስፋዬ ከመከላከያ ተከላካዮች መካከል ሾልካ በመውጣት በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከመስመር በሚሻገሩ እንዲሁም በቀጥተኛ ኳስ ለማጥቃት ጥረት ያደርጉ የነበሩት መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ ሳጥን መድረስ ቢችሉም እድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን አፈፃፀማቸው ጥሩ አልነበረም ፤ በ23ኛው ደቂቃ አዲሱ አቱላ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ ኢማኑኤል ላርያ በግንባሩ ገጭቶ ከሞከረው ውጭ አደገኛ አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ31ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ኃይሉ ላይ ዳዊት ማሞ በሰራው ጥፋት ሀዋሳ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን በደቂቃዎች ልዩነት መከላከያዎች በ38ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ላይ ዳንኤል ደርቤ በሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ከሰሞኑ ከጉዳት የተመለሰው ኡኩቱ ኢማኑኤል ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰችን ግብ ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት ከማምራታቸው በፊት አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሰመረ ሃፍታይ በሰከንዶች ልዮነት መሀመድ ሙንታሪ ኳስ ለማስጀመር ባደረገው ጥረት በፍጥነት ውሳኔ አለመወሰኑን ተከትሎ ሰመረ ደርሶ ኳሱን በማቋረጥ ቡድኑን አቻ ያደረገችን ግብ በማስቆጠር መከላከያዎን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኃላ ዳግም የተነቃቁ የሚመስሉት ሀዋሳዎች በ57ኛው ደቂቃ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ዮናስ ማርቆስ አወዛጋቢ በነበረ ውሳኔ ኢማኑኤል ላርያ ኤፍሬም አሻሞ ለቡድን አጋሩ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት መስፍን ታፈሰ በማስቆጠር ቡድኑን ደግም መሪ ማድረግ ችሏል።

አስገራሚ መልክን ይዞ መካሄዱን በቀጠለው ጨዋታ በ73ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አስቀድሞ በመጀመሪያ አጋማሽ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የሀዋሳ ከተማው ጋናዊ የመሀል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ በረጅሙ የተላከን ኳስ በእጅ በመንካቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ከላውረንስ ቀይ ካርድ በኃላ ሀዋሳ ከተማዎች ይበልጥ ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ተስበው በመከላከል ውጤቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በ86ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፀጋሰው ድማሙ ኡኩቱ ኢማኑኤል ላይ በሰራው ጥፋት መነሻነት ፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጥባቸውም የፍፁም ቅጣት ምቱን ቢኒያም በላይ ቢመታም መሀመድ ሙንታሪ በግሩም ሁኔታ በማዳን ቡድኑ ውጤቱን እንዲያስጠብቅ በማድረግ በእሱ ስህተት የተቆጠረችውን ግብ አካክሷል።

በዚህ ያለበቃው ጨዋታው በ88ኛው ደቂቃ ላይ አሌክስ ተሰማ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ በጨዋታው አምስተኛ የፍፁም ቅጣት ምትን ሀዋሳ ከተማ ቢያገኙም አዲስዓለም ተስፋዬ የመታውን የፍፁም ቅጣት ምትን ክሊመንት ቦዬ ሊያድንበት ችሏል።

በክስተቶች የተሞላውን ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 26 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ አንሰው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ተሸናፊው መከላከያ ደግሞ በ17 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።

ያጋሩ