[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
አስገራሚ ምሽት ከነበረውና ሀዋሳ መከላከያ ላይ ወሳኝ ድል ካስመዘገበበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ
“ለተመልካች ጥሩ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል። በውጤት ደረጃ ስትመለከተው ለእኛ ጥሩ አደለም። የማይሆኑ ስህተቶችን እየሰራን በመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃ ሁለት ጎሎችን ሰጥተን ነበር። ልንከላከላቸው የምንችላቸው ስህተቶች ነበሩ። ከሁለት ለዜሮ ተነስተን አቻ ሆነናል። ፍፁም ቅጣት ምት የእግርኳሱ አንድ አካል ነው። ማንም መሳት ይችላል፤ መሳቱ አዲስ ነገር አይደለም። ብቻ ለሁለታችንም ጥሩ ጨዋታ ህዝብን የሚያስደስት ጨዋታ በብዛት ወጣቶች የተንቀሳቀሱበት ማለት ይቻላል።
ስለ ዳኝነት ውሳኔ
ስለ ዳኛ ተናግሬ አላቅም፤ አሁንም አልናገርም። ቴሌቪዥን ስላለ በግልፅ ስለሚታዩ ስለዳኛ ማውራቱ ለዳኛ ኮሚቴ መተው ነው። እያንዳንዱን አስራ አራት ጨዋታ እያወጣን ቪዲዮ ኤዲት እየተደረጉ ቢወጡ በርካታ ነገሮች አሉባቸው። ስለዚህ የዳኛውን በተመለከተ ኮሚቴዎች ስላሉ ለራሳቸው ሲሉ ለጨዋታው ጥራት ሲባል ማድረግ የሚገባቸውን ቢያደርጉ ዓለም የሚያየው ውድድር ስለሆነ ትዝብት ውስጥ እንዳይከተን ለፊፋም ለካፍም ለሌላው ራሳቸው እያሰቡበት ማረም የሚገባቸውን ቢያርሙ ጥሩ ነው ብዬ እናገራለው። ከዛ ውጭ ስለ ዳኝነት መናገር አልፈልግም።
የቡድኑ ክፍተት
ክፍተት ኖሮ አይደለም፤ ስህተቶች ናቸው። ማጥቃቱንም መከላከሉንም አድርገናል። ከእረፍት በፊት ያገቡብን ኳሶች በራሳችን ስህተቶች፣ በቆሙ ኳሶች በፍፁም ቅጣት ምት ነው ሁለቱ ጎሎች የተቆጠሩብን። ከእረፍት በኋላ ብዙም የፈጠሩት ሙከራ አልነበረም። ግን የእግርኳሱ አካል ነው። በመጫወት ደረጃ ጥሩ ተጫውተናል ውጤቱ ባይቀናንም።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ሀዋሳ ከተማ
ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ
ቡድኔ ዛሬ እውነት ለመናገር እንደፈለግኩት አይደለም። የምንሳሳታቸው ኳሶች ከእኛ ተከላካይ የማይጠብቅ ነው። በዚሁ አጋጣሚ ዳኛውን ላደንቅ እወዳለው። ምክንያቱም ድፍረቱ የሚታይ ነገር ነው። ትክክለኛ ውሳኔ ነበር የሚሰጠው። እንዲህ ያለ ነገር ሊበረታታ ይገባል እላለሁ። ከዚህ በመቀጠል የተከላካይ ቦታ ተጫዋቾች ዛሬ መረጋጋት የሚባል ነገር የለም። የምንሰራቸው ስህተቶች በጣም ዋጋ የሚያስከፍሉ ነበሩ። እድለኞች ስለነበርን እንጂ ነጥብ ጥለን የምንወጣበት ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ የእነርሱ ተከላካዩች ስህተት ቢሰሩም የእኛ ግን ለየት ይላል። በደንብ መታረም ያለበት ነገር ነው ብዬ የማስበው። ቡድኔን እንደፈለኩት ባላገኘውም ዋናው ሦስት ነጥብ ነው የሚፈለገው ተሳክቶልናል።
ፍፁም ቅጣት ምት ለመምታት ስለነበረው ውዝግብ
የመጀመርያ መቺ አዲስዓለም ነው። ብሩክ አጥቂ ስለሆነ እርሱ እንዲመታ ፈቅዶለት ነው ሁለተኛ መቺ እርሱ ነው። ተባረክ ያደረገው ነገር ትልቅ ስህተት ነው እርሱ መቺ አይደለም። ምርጫችንም አይደለም። እርሱ መጠየቅ በሚገባን መጠን እንጠይቃለን። ዞሮ ዞሮ እርሱም ስሜት ነው። ጎል አላገባም ጎል አግብቶ ወደ ጎል አግቢነት ለመግባት ነው። ተጫዋቾቹም እርሱ እንዲመታ ፈልገው ነበር። ለኔ ግን የመጀመርያ መቺያችን አዲስዓለም ነው። እርሱም ስቷል። ይሄን እናስተካክላለን። ያው እንዳንዴ ይፈቃቀዳሉ። አንዱ አንዱ እንዲመታ ይህ የቡድኑን መንፈስ ያሳያል። ይህ በቀላሉ የሚስተካከል ነው።
ስለ ላውረንስ ስህተት
የራሱን ስህተት ለመሸፈን ያደረገው ነገር ነው። መጀመርያም ሲሳሳት የነበረው እርሱ ነው። የእርሱ አቋቋም ትክክል ስላልሆነ መልበሻ ክፍልም የተናገሩኩት እርሱን ነበር። በእርሱ የሚመጡ ኳሶች አቋቋሙ ትክክል ስላልነበር ያንን ሽፋን ለመስጠት ነው። ጎሉ ሊገባ እንደሚችል አስባለው። ስለማይደርስበት ነው ይሄን ያደረገው ከእርሱ የማይጠበቅ ስህተት ነው። ብቻ ይህንንም እናርማለን። በእግርኳስ እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል።
ስለ ደረጃ ማሻሻላቸው
ባለፈውም ተናግሬዋለሁ። በድሬደዋ ቆይታችንን በድል ጀምረነዋል። አንድ ጨዋታ ይቀራል። በድልም እንጨርሳለን ብዬ አስባለው። ግስጋሴያችን አይቆምም። ፕሪምየር ሊጉ እስካለ ድረስ እስከ መጨረሻው እንታገላለን። ያለብንን ደካማ ጎኖቻችንን ሁለተኛው ዙር ላይ ተከላካይ ቦታ ላይ በደንብ አስተካክለን መምጣት ይኖርብናል። ይህ ትልቅ የቤት ስራ ነው። ከዛ ውጭ የዛሬው እንቅስቃሴያችን እንደበፊቱ አልነበረም። ወደዛ መመለስ አለብን። ግስጋሴያችን ይቀጥላል።