​አዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አሠልጣኙን በቋሚ ዋና አሰልጣኝነት ሾሟል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከሁለተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ጀምሮ አዲስ አበባን በጊዜያዊ አሠልጣኝነት ሲመሩ የነበሩት አሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ የዋና አሠልጣኝነት ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ተሰጥቷቸዋል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከሁለተኛው የሊግ እርከን ወደ ዋናው የሀገሪቱ የውድድር እርከን በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር አማካኝነት ያደጉት አዲስ አበባ ከተማዎች የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከባህር ዳር ከተማ ጋር አድርገው ሦስት ለምንም የተሸነፉ ሲሆን ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ሊያደርጉ ሰዓታት ሲቀረው አሠልጣኝ እስማኤል እና የቡድን መሪው አቶ ሲሳይ ፀብ ውስጥ ገብተው አሠልጣኙ እንደታገዱ ይታወሳል። ከእግዱ በኋላም ክለቡ ጉዳዩን መርምሬያለው በማለት ከአሠልጣኙ ጋር እንደተለያየ አይዘነጋም።

በዚህ ሂደት ከሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ክለቡን ከግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ መሠረት ጋር በመሆን ሲያሰለጥኑ የነበሩት አሠልጣኝ ደምሰው ለበርካታ ቀናት ሀላፊነታቸው በጊዜያዊነት ስም ቀጥሎ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የክለቡ ቦርድ በዋና አሠልጣኝነት እንዲሰሩ ውሳኔ አሳልፏል። 

አሠልጣኝ ደምሰው የተሰጣቸውን ሀላፊነት ዛሬ ከሲዳማ ጋር እንዲሁም በቀጣይ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደተለመደው ከግብ ጠባቂዎች አሠልጣኙ መሠረት ወልደማርያም ጋር በመሆን ከከወኑ በኋላ በሁለተኛው ዙር ረዳት አሠልጣኞችን በራሳቸው አማራጭ ወደ ስብስቡ እንደሚያመጡ ሰምተናል።