በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከዲ.ሪ. ኮንጎው ክለብ ቲፒ ማዜምቤ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ተወካዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሉቡምባሺ ይገኛል፡፡ ፈረሰኞቹ ዕረቡ ዕለት ቦሌ በሚገኘው የመለማመጃው ሜዳ አዲስ አበባ ላይ የመጨረሻ ልምምዳቸው የሰሩ ሲሆን ነገ በስታደ ቲፒ ማዜምቤ የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሰለፍነው ዕሁድ ባህርዳር ላይ በ60ሺህ ደጋፊዎች ፊት ከማዜምቤ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-2 መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ረቡዕ በክለቡ የልምምድ ስፍራ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከፈረሰኞቹ አማካይ ናትናኤል ዘለቀ ጋር ባደረገችው ቆይታ ጨዋታውን ለማሸነፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጿል፡፡
” ለመልሱ ጨዋታ በተሻለ መንፈስ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ጥሩ ልምምዶችን ሰርተናል፡፡ በጨዋታው የተሻለ ነገር እናደርጋለን ብለን እናስባለን፡፡ ” ብሏል፡፡
የውድድር ዘመኑን በተጠባባቂ ወንበር በመቀመጥ የጀመረው ናትናኤል ወደ ቋሚ አሰላለፍ የተመለሰበትን ምስጢር ያብራራል፡፡ “ዓምና ከብሄራዊ ብድን ጨዋታዎች በኃላ እግሬ ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር፡፡ በዚያም የተነሳ ከጨዋታ ርቄ ነበር፡፡ ከጉዳት ካገገምኩኝ በኃላ ባሉት ጊዜያት ጠንክሬ ከቡድኔ ጋር ልምምድ እየሰራው ወደ ቋሚ አሰላለፍ ልመለስ ችያለው፡፡ ”
በባህርዳሩ ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ናትናኤል በሉሙምባሺ ምን ማድረግ እንደሚገባቸውም ይናገራል፡፡ ” በሙሉ የራስ መተማመን ወደ ሜዳ መግባት አለብን ብዬ አስባለው፡፡ በሜዳችን አቻ ነው የወጣነው፡፡ ስለዚህም የግድ ግብ ማስቆጠር አለብን፡፡ ቲፒ ማዜምቤዎች ከፍተኛ ልምድ አላቸው፡፡ ቡድኑም በጣም በትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ያንን ተቋቁመን አሰልጣኛችን በሚሰጠን መመሪያ መሰረት የተሻለ ስራዎችን ሰርተን ያለንን ሃይል በሙሉ ሰጥተን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንጥራለን፡፡ “