​የአሠልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ቀልብ ሳቢው ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ ሀሳብ ተቀብሏል።

ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በነበረው ዳኝነት ደስተኛ ነህ?

የእነርሱ ውሳኔ ነው። የእነርሱን ውሳኔ አከብራለው። ሰው ናቸውና የሆነ ነገር ሊሳሳቱ ይችላሉ። ያንን አሁን መናገር አልፈልግም።

ተጋጣሚን ለማስከፈት ስለወሰዱት እርምጃ?

በሁለተኛው አጋማሽ ምንም ነገር ወደእኛ አልመጡም። እኛ ነበር ጫና የፈጠርነው። የግብ ማግባት ዕድሎችንም አግኝተናል። ጎልም የሆነ ነገር አግኝተናል። አላውቅም። ምስሉን ሳየው ጎል ነው አይደለም የሚለውን ልመሰክር እችላለሁ። ግን በአጠቃላይ ጠንካራ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ጨዋታ እንደነበር ሳልደብቅ መናገር እፈልጋለው።


የቡልቻ ጉዳት እና ተፅዕኖ?

ተጫዋቹ ቀጥታ ኳስ ለመምታት ገባ። አሟሙቋል ግን ቀጥታ ወደሹት ስለገባ ነው። ምንም እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይገባ ስለሆነ ይህ አደጋ ሊከሰት ይችላል። እሱን ወደ ሜዳ ያስገባንበት እቅድ ነበረን። እሱ ጠንካራ ተጫዋች ስለሆነ ኋላቸውን ለማስከፈት ነበር። ግን በጉዳት ወጣ። የተካነውም ወጣት ተጫዋች ተመሳሳይ በመስመር እንዲጫወት ነበር ያረግነው። ጥሩ ነገሮች አግኝተናል። ግን እግርኳስ ነው።

በመጨረሻ ደቂቃዎች አጥቂ ስለማብዛታቸው?

መጨረሻ አካባቢ ጎሎችን ከመፈለግ ነው። እነሱ ጎላቸውን ዘግተው ደቂቃዎችን አባክነው ለመውጣት ነበር ያሰቡት። እንዳያችሁት በሁለተኛው አጋማሽ በምንም አይነት መንገድ ወደእኛ አልመጡም። በመስመር ላይ ጥፋቶች እንዲሰራባቸው ነበር የሚመጡት። ግን እኛ ብዙ አጋጣሚዎችን አግኝተን አልተጠቀምንበትም። ይሄ የራሳችን ስህተት ነው። በዚህ ላይ ሰርተን እንመጣለን።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለተመዘገበው ውጤት?

ጊዮርጊስ ጠንካራ ቡድን ነው። ይታወቃል። ሊጉን የሚመራ ቡድን ነው። ስለዚህ አንድ ነጥብ ፍትሀዊ ነው። ከምንም ይሻላል። ሁለታችንም ተመሳሳይ አቀራረብ ነው ይዘን የገባነው። እነርሱም ከእኛ ጀርባ በረጃጅም ኳሶች ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። እኛም እንደዚሁ ከሜዳችን ወጥተን ለማጥቃት ጥረት አድርገናል። እነሱ ከእኛ የተሻሉ ናቸው። የተሻሉ የጎል አጋጣሚ ፈጥረዋል። በተለይ በመጨረሻዎቹ አካባቢ። ግን በአጠቃላይ አንዱም ነጥብ ከምንም የተሻለ ነው የሚሆነው። ፈጣሪ ይመስገን።


በጨዋታ መሐል ወርቅይታደስ እና ተካልኝን ቦታ ስለቀየሩበት ምክንያት?

ከባላጋራ ተጫዋቾች ባህሪ አንፃር ነው። አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾች የራሳቸው ብቃት አላቸው። ከዚህ አንፃር ታክቲካል ለውጥ ነው ያደረግነው። ከሞላ ጎደል ቅያሬያችን ጥሩ ነበር። በቀኝ በኩል ያለው ተጫዋች ኳስ ሲገፋ የእኛን ተጫዋች የግራ እግር ያገኛል። በዛም ጋር የፈለግነው ነገር ነበር። ቦታን እየፈለጉ ለማጥቃት ይፈልጉ ነበር። ይሄንን ቦታ ለመዝጋት ነበር ጥረቱ። እርሱም ተሳክቷል።

ስለዳኝነት ውሳኔዎች?

ይህ የእነርሱ ስራ ነው የሚሆነው። እዚህ ጋር ስንሆን የተለያየ ባህሪ እናሳያለን። የሚመለከተው አካል ስላለ ችግር ካለ እነርሱ ያዩታል።

ቡና እና ጊዮርጊስ ላይ በድምሩ ስላገኙት 4 ነጥብ…? 

የእኛ ትልቁ ነጥብ የጀመረው ከሲዳማ ቡና ጋር ያገኘናት አንድ ነጥብ ናት። ከዛ በኋላ ተከታታይ ነጥቦችን እያገኘን ስንመጣ ነበር። አሁንም በኢትዮጵያ ታላላቅ ከሚባሉ ክለቦች 4 ነጥብ ማግኘት ትልቅ ስኬት ነው። በቀጣይም ነጥቦችን እያገኘን ካለንበት ከፍ ብለን የተሻለ ደረጃ ላይ ለመጨረስ እንሞክራለን።