[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሰባት ጨዋታ በኃላ ግብ ባስተናገዱበት ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከአዞዎቹ ጋር አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ጉዳት ባስተናገደው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ምትክ ቸርነት ጉግሳን ሲተኩ በተመሳሳይ አርባምንጭ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡናን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ሀቢብ ከማልን በወርቅይታደስ አበበ ተክተው ወደ ጨዋታው ቀርበዋል።
ሁለት ቀጥተኛ አጨዋወትን ምርጫቸው ያደረጉ ቡድኖች መካከል በተደረገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅሙ በሚጣሉ ኳሶች የተጋጣሚን ሳጥን ለመፈተሽ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።
17ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል የነጠቁትን ኳስ ፀጋዬ አበራ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ይዞ ለመግባት የሞከረውን ኳስ ለማስጣል የሞከረው ጋቶች ፖኖም በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትን ኤሪክ ካፓዬቶ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ለመሆን መቸገሩን ተከትሎ ከወትሮው በተሻለ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን መስረተው ለመውጣት ሆነ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን ይህም ሂደት በተለይ ወደ መሀል ሜዳ ሲቃረብ ለአርባምንጮች ጫና እንደ መነሻም ሲሆን ታዝበናል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ ይበልጥ አርባምንጭ ከተማዎችን ሳጥን መጎብኘት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአቤል ያለው እና እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጥረታቸው ግን በ30ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል ፤ አሸናፊ ፊዳ አቤል ያለው በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እስማኤል ኦሮ-አጎሮ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።
የመጀመሪያ አጋማሽ እየገፉ በሄደ ቁጥር ይበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው የተሻሉ እየሆኑ የመጡ ሲሆን አጋማሹ ሊጠናቀቅ የሰከንዶች ብቻ እድሜ በቀረበት ወቅት አቤል ያለው በግሩም የማጥቃት ሽግግር ወደ አርባምንጭ ሳጥን በግል ጥረቱ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሯት ሳምሶን አሰፋ ባዳነበት ሙከራ አጋማሹ ፍፃሜውን አድርጓል።
አርባምንጭ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በተወሰነ መልኩ አዎንታዊ አጀማመር ያደረጉ ቢመስልም በሁለቱም አጋማሾች በክፍት ጨዋታ እድሎችን ለመፍጠር ግን ተቸግረው ተመልክናል።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሀቢብ ከማል ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ላይ ፍቃዱ መኮንን በኩል ካደረጉት ሙከራ ውጭ በአጋማሹ አርባምንጭ ከተማዎች በግሩም የቡድን ስራ ሲከላከሉ የነበሩበት መንገድ የሚደነቅ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም የአርባምንጭ ከተማን የመከላከል ውቅርን ግን ጥሰው ለመግባት ተቸግረው ተስተውሏል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ኦሮ-አጎሮ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችበት አጋጣሚ ውጭ ተደጋጋሚ እድሎችን ከተሻጋሪ ኳሶች ተደጋጋሚ እድሎችን በተለይ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች መፍጠር ቢችሉም የአርባምንጭ የመከላከል ውቅር የሚበገር አልሆነም።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተሻጋሪ ኳሶች ጫናቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የተሳሳተ የመስመር ዳኝነት ውሳኔ ተከስቶ ፈረሰኞቹ መሪ የሚሆኑበት እድል ሳይሳካ ቀርቷል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በ28 ነጥብ ሊጉን በመምራት ሲቀጥሉ አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በ17 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።