ጌታነህ ከበደ ዛሬ ልምምዱን ሲጀምር ዋሊድን ለማካተት የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአልጄርያው ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ቀጥሎ ዛሬ ረፋድ ላይም በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምድ አድርጓል፡፡ ትላንት አዲስ አበባ የገባው ጌታነህ ከበደም የመጀምርያ ልምምዱን ከቡድኑ ጋር አድርጓል፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ ልምምድ እየሰራ የሚገኝ 17ኛ ተጫዋችም ሆኗል፡፡

ታፈሰ ተስፋዬ ፣ ሙሉአለም ጥላሁን ፣ ስዩም ተስፋዬ እና ሳላዲን ሰኢድ ከቡድኑ ውጪ በመሆናቸው እንዲሁም 4 ተጫዋቾች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ኮንጎ የሚገኙ በመሆናቸው ምክንያት በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከተመረጡት 24 ተጫዋቾች መካከል በአሁኑ ሰአት በብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙት ሶስት ግብ ጠባቂዎችን ጨምሮ 17 ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ይህም ዋልያዎቹ ወደ አልጄርያ ይዘዋቸው ሊጓዟቸው ከሚችላቸው 18 ተጫዋቾች ያነሰ ቁጥር ነው፡፡ ሆኖም በጉዳት ምክያት ከቡድኑ በወጡት ተጫዋቾች ምትክ እስካሁን ተጨማሪ ተጫዋቾች ያልተጠሩ ሲሆን በመጪው ሰኞ ወደ አልጄርያ እስኪጓዙ ድረስ ተጨማሪ ተጫዋቾች ይካተቱ አይካተቱ የታወቀ ነገር የለም፡፡

IMG_1305

በተያያዘ ዜና ዋሊድ አታ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀል የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ ዋሊድ ከአንድ ወር በፊት የቱርኩ ጊንሰልቢሪጊን ለቆ ወደ ስዊድን በመመለስ ለኦስትራዳ ከፈረመ ወዲህ በተከላካዩ እና በፌዴሬሽኑ መካክል የነበረው ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ኢትዮ ስፖርት ድረ-ገፅ እንደዘገበው ለዋሊድ የተላከው የጥሪ ደብዳቤ የደረሰው ለአዲሰ ክለቡ ሳይሆን ከወራት በፊት በስምምነት ለተለያየው የቱርኩ ጌንሰልብሪጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በብሄራዊ ቡድኑ አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ሰኞ በ10፡00 ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ የታወቀ ሲሆን በዛው እለት ምሽት 04፡00 ደግሞ ወደ አልጄርያ ጉዞውን ያደርጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *