​ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባጅፋር ከ ወልቂጤ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ የሚከተሉት ሀሳቦች ተቀምጠዋል።

የሊጉ ሁለተኛ ምዕራፍ ውድድር በድሬዳዋ መደረጉ የተመቸው የሚመስለው ጅማ አባጅፋር ለበርካታ ቀናት ከነበረበት የደረጃው ግርጌ ለመራቅ እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ያለውን ተስፋ ለማለምለም ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻ ላይ ያሳካውን ድል ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባል። ከጅማ በተቃራኒው በድሬዳዋ ስታዲየም እስካሁን ድል ማድረግ ያልቻለው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት የአሠልጣኝ ለውጥ አድርጎ ያሳየውን የእንቅስቃሴ መሻሻል በውጤት ለማጀብ ነገ ታትሮ ጅማን ሦስት ነጥብ ለመንጠቅ እንደሚጥር ይገመታል።

ለበርካታ ቀናት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጦ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ አስር ሳምንታትን መጠበቅ ግድ ብሎት የነበረው ጅማ አባጅፋር ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ለወትሮ ከግብ ጠባቂ ቦታ ውጪ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ያለመቀናጀት ችግር የነበረበት ስብስቡም በርካታ ተጫዋቾችን በየጨዋታው እየቀያየረ የማሸነፍ ስልቱን ከፈለገ በኋላ አሁን ጠንካራ አሰላለፉን ያገኘ ይመስላል። ከምንም በላይ በግብ ጠባቂ ቦታ አላዛር፣ በተከላካይ መስመር ኢያሱ እና የአብስራ፣ አማካይ መስመር ላይ ደግሞ መስዑድ እና ዳዊት እንዲሁም በአጥቂ ቦታ መሐመድኑር እና እዮብ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች እየሆኑ ይገኛል። አልፎ አልፎ ለኳስ ቁጥጥር ፍላጎት የሚያሳየው ቡድኑም በድቻው ጨዋታ ኳሱን ለተጋጣሚ ትቶ ለመልሶ ማጥቃት ማስተማሪያ ምሳሌ የሚሆን አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ እርሱንም ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጣፋጭ ድል ተጎናፅፏል። እርግጥ የድቻው ጨዋታ ቡድኑ በዘጠነኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ ሁለት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ብቻ ካደረገ በኋላ ዝቅተኛ የግብ ማግባት ዕድሎችን (4) የፈጠረበት ሆኖ ቢያልፍም በግማሽ ሰዓት አካባቢ ያገኘውን ጎል አስጠብቆ የወጣበት እና ጨዋታውን ለራሱ አድርጎ የጨረሰበት መንገድ መልካም ነው። ነገም ቡድኑ ከኳስ ውጪ እንደሚያሳልፍ ሲጠበቅ ፈጣኖቹን አጥቂዎች ከተከላካይ ጀርባ እንዲሮጡ በማድረግ ግብ ለማግኘት እንደሚጥር ይገመታል።

አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በጻውሎስ ጌታቸው ምትክ ባሳለፍነው ሳምንት ያመጣው ወልቂጤ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ግብ ቢለያይም ብዙዎችን ያስገረመ ብቃት ነበር በሜዳ ላይ ያስመለከተው። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ እጅግ ከፍተኛ ተነሳሽነት በማሳየት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ኖሮት ሲጫወት ያስተዋልን ሲሆን ኳስ በሚነጠቅበትም ሰዓት ወዲያው አፀፋዊ ምላሽ በመሰንዘር ኳሱን ዳግም ለመንጠቅ ሲታትር ነበር። ከዚህም መነሻነት የሲዳማ ተጫዋቾች በወልቂጤ አጨዋወት ቅኝት እንዲገቡ የሆነ ሲሆን የቡድኑም አጨዋወት አማካይ መስመር ላይ ተቆርጦ ነበር። በወልቂጤ በኩል የነበረው የጨዋታ ግለት በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባይቀጥልም በመጀመሪያው አጋማሽ ከታየው ጥቅም መነሻነት ነገም ይህ የጨዋታ ሀሳብ በሜዳ ላይ ሊተገበር ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ረመዳን እና ተስፋዬ እጅግ ገፍተው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንዲገኙ በማድረግ የግብ ምንጭ ለማግኘት የሚደረገው ጥረትም ለጅማዎች ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል። ከዚህ ውጪ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው ጌታነህ እና ምርጥ ብቃቱን እያገኘ የሚመስለው ጫላ እንቅስቃሴ ዋናኛው የቡድኑ ጠንካራ ጎን ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንካራ እና ደካማ ጎን ያላቸው ናቸው። በወረቀት ላይ ባለሜዳ የሆነው ጅማ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስቆጠረ የፊት መስመር ባለቤት ሲሆን ግቡን የሚጠብቅለት ወጣቱ የግብ ዘብ ደግሞ እጅግ ጠንካራ ብቃቱ ላይ በመገኘት በተቻለው አቅም ግቦችን እንዳይቆጠሩ ይጥራል። በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ካስተናገዳቸው 15 ግቦች 9ኙ ሲቆጠሩ በግብ ብረቶቹ መሐል የነበረው ሰዒድ ከፍተኛ የውሳኔ እና የትኩረት ማነስ ችግር ላይ ሲገኝ ከፊት ደግሞ ቡድኑ ካገባቸው 11 ጎሎች 8ቱን ያስቆጠሩት ጌታነህ፣ አህመድ እና ጫላ ደግሞ ለተጋጣሚ ምቾት የሚሰጡ አይደለም። በዚህ ሂደት ነገ በሁለቱ ጫፍ እና ጫፍ የሜዳ ክፍሎች የሚኖሩ ቅፅበቶችም በጨዋታው መነጋገሪያ እንደሚሆኑ ይታሰባል።

ጅማ አባጅፋር በነገው ፍልሚያ በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የለም። በትናንትናው ዕለት እንዳስነበብነው ሚኪያስ ግርማ፣ አስናቀ ሞገስ እና ዮሐንስ በዛብህ በክለቡ እግድ ስለተላለፈባቸው ከጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ውጪ ሆነዋል። በወልቂጤ በኩል ምንም የጉዳት ዜና አለመኖሩ ተሰምቷል። ዮናስ በርታ ግን በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ነው።

እያሱ ፈንቴ ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ለመምራት ሲመደቡ ሸዋንግዛው እና ደረጀ አመራ ረዳት አባይነህ ሙላት ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ያገለግላሉ።


የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ሳይጨምር ሁለት ጊዜ በሊጉ ተገናኝነተው አንዱን ወልቂጤ 2-1 ሲያሸንፍ በሌላኛው ያለግብ አቻ ተለያይተዋል።


ግምታዊ አሠላለፍ


ጅማ አባጅፋር (4-3-3)

አላዛር ማርቆስ

በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድማገኝ ማርቆስ

ዳዊት እስቲፋኖስ – አዛህሪ አልመሃዲ – መስዑድ መሐመድ

ዳዊት ፍቃዱ – መሐመድኑር ናስር – እዮብ አለማየሁ


ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ሀብታሙ ሸዋለም –  በኃይሉ ተሻገር

አብዱልከሪም ወርቁ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ