ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ14ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በማስመልከት ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የመጨረሻ ሽንፈቶቻቸውን በጅማ አባ ጅፋር ያስተናገዱት ድቻ እና ሆሳዕና 14ኛውን የጨዋታ ሳምንት ያሳርጋሉ። ከደካማ አጀማመሩ ቀስ በቀስ እያገገመ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ መልስ የሰንጠረዡን አጋማሽ ለመሻገር ወደ ሜዳ ይገባል። ወደ ላይኛው ፉክክር የተጠጋው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ትናንት ድል የቀናው ሀዋሳ ከተማ እና ዛሬ ነጥብ የጣለው መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ለመቀነስ ውጤቱን አጥብቆ ይፈልገዋል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች የባላጋራን የመስመር ጥቃቶች በመቋቃም በኩል ተመሳሳይ ጥንካሬን ማሳየታቸው የነገው ጨዋታ የኮሪደሮች እንቅስቃሴ ላይ እንድናተኩር ያደርገናል። ወላይታ ድቻ በተለይም መከላከያን ሲያሸንፍ ግራ እና ቀኝ ባለውን የሜዳ ክፍል የሚነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማፈን ጥሩ አተገባበር ነበረው። ሀዲያ ሆሳዕናም በዚህ ረገድ ጠንካራ የሚባለው ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቋቋመበት መንገድ በጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ትልቅ ድጋፍ አድርጎለታል። በነገው ጨዋታ ግን በሦስት ተከላካዮች የሚጀምር አደራደርን የሚጠቀመው ቡድኑ ለመስመር ተመላላሾቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ኃላፊነትን በመስጠት እስከ ድቻ ሳጥን ዘልቀው ኳሶችን ወደ ሳጥን እንዲያደርሱ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በቦታው ቅድሚያ ለጥንቃቄ የሚሰጠው የወላይታ ድቻ ተሰላፊዎች ይህን የማጥቃት ሂደት ለማክሸፍ እና በተለያዩ ምክንያቶች አማራጩ በጠበበው የሆሳዕና ሦስቱ የመሀል ተከላካዮች ግራ እና ቀኝ ረዘም ባሉ ኳሶች ለመግባት የሚያደርጉት ጥረትም በቦታው ጥሩ ፍልሚያ እንድንመለከት ሊያደርገን ይችላል።

በሌላው ፉክክር የአማካይ ሜዳ ላይ የተሻለ ኳስ የመመስረት ፍላጎት ኖሮት የሚታየው ሀዲያ ሆሳዕና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። በዚህ ረገድ በጅማው ጨዋታ ፈጣሪ አማካዮችን ለመቆጣጠር ተቸግሮ የነበረው ወላይታ ድቻ ወደ ግብ በመቅረብ ከቡድኑ የመስመር ጥቃት መነሻነት ዘግይተው በመድረስ ሙከራዎችን ማድረግ የሚያዘወትሩትን የሀዲያ ሆሳዕና አማካዮች የመቆጣጠር ፈተና ይጠብቀዋል። ሀዲያ ሆሳዕናም ከጊዮርጊሱ ጨዋታ በተለየ እንደወትሮው የፊት አጥቂዎቹን ቁጥር ሁለት በማድረግ በቦታው ቅብብሎችን ለመከወን የሚረዳ የቁጥር ብልጫን ለመግኘት በመሞከር ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።

ግብ በማስቆጠር በኩል እምብዛም ያልተራራቀ ቁጥር ያላቸው ቡድኖቹ እስካሁን የአቻ ውጤት በማያውቀው ግንኙነታቸው ነገም የፊት መስመራቸውን ስልነት አብዝተው ይፈልጋሉ። በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ በቁጥር በርካታ ያልሆኑ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ግብነት መቀየር የሦስትዮሽ ጥምረት ካለው የወላይታ ድቻ የፊት መስመር ጥሩ አጋጣሚን ወደ ግብነት የመቀየር ንፃሬ ይጠበቃል። ከአማካይ እና የመስመር ተሰላፊዎች ጋር ከተጋጣሚው በተሻለ ለቅብብሎች የሚገናኘው የሆሳዕና የፊት መስመርም ከግብ ባለፈ በእንቅስቃሴ ወደ ሳጥን ለሚቀርቡ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች ክፍተትን የመፍጠር ኃላፊነት እንደሚኖርበት ይጠበቃል።

ሀድያ ሆሳዕና እያሱ ታምሩ ፣ መላኩ ወልዴ እና ኤፍሬም ዘካሪያስን በጉዳት ሲያጣ በቅርቡ የተሞሸረው ፍሬዘር ካሳ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል። ወላይታ ድቻ ግን ያለጉዳት እና ቅጣት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

በጨዋታው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሀል ፋሲካ የኃላሸት እና ዳዊት ገብሩ በረዳትነት ዮናስ ማርቆስ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን በአራት የሊግ ጨዋታዎች የተገናኙት ተጋጣሚዎቹ ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል። ሀዲያ ሆሳዕና ሰባት ወላይታ ድቻ ደግሞ ስድስት ግቦችንም አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ወንድወሰን አሸናፊ

በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

አዲስ ህንፃ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ

ቃልኪዳን ዘላለም – ስንታየሁ መንግስቱ – ምንይሉ ወንድሙ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

መሳይ አያኖ

እሸቱ ግርማ – ቃለዓብ ውብሸት – ኤልያስ አታሮ

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ሄኖክ አርፌጮ

ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ

ያጋሩ