​ሪፖርት | አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ወልቂጤ ጅማን ረቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወልቂጤ ከተማ 10 ነጥብ ብቻ ያለው ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመቱ አስረኛ ሽንፈቱን እንዲያስተናግድ አድርጎ በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።             

ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን በእዮብ ዓለማየሁ ብቸኛ ጎል አሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ጅማ አባ ጅፋሮችም ሆኑ ከአዲስ አሠልጣኝ ቅጥር በኋላ ከሲዳማ ቡና ጋር ተጫውተው ያለ ግብ አቻ የተለያዩት ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው የተጠቀሙትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳይለውጡ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ቡድኖቹም ጨዋታውን ለመጀመር ወደሜዳ ሲገቡ ከቀናት በፊት ህልፈቱ የተሰማው የቢሾፍቱ ከተማ በመሐል ተከላካይነት ኖህ ደሳለኝን የሚያስብ ምስል ይዘው ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ የተስተዋለበት ነበር። በአንፃራዊነት የተሻከ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ወልቂጤ ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ በመታው ነገርግን ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በተቆጣጠረው ኳስ መሪ ለመሆን ጥረው ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጅማዎች ሳይጠበቅ አደጋ ፈጥረዋል። በዚህም ከመሐል ሜዳ የተሻገረውን ረጅም ኳስ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ለማውጣት ሲሞክር አምልጦት አደጋ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን የመሐል ተከላካዩ ዋሀብ አዳምስ ደርሶ ግን ከግብነት ታድጎታል።

ቀስ በቀስ ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የያዘው ፍልሚያ የጠራ የግብ ማግባት ዕድል ሳይፈጠርበት ግማሽ ሰዓት ሞልቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ በግራ መስመር ወደ ወልቂጤ የግብ ክልል ያመሩት ጅማዎች ከሳጥኑ ጫፍ በዳዊት እስቲፋኖስ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ሰዒድ እና የግቡ ቋሚ ተባብረው ኳሱን አውጥተውታል። ወልቂጤዎች ደግሞ በ37ኛው ደቂቃ ጫላ ተሺታ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በረመዳን የሱፍ መተውት ግብ ለማግኘት ሞክረው አዛህሪ መልሶታል። ከደቂቃ በኋላ ግን ካልታሰበ ቦታ ግብ አግኝተው መሪ ሆነዋል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተስፋዬ ነጋሽ መሐል ሜዳ ላይ ከሀብታሙ ሸዋለም የተረከበውን ኳስ እየገፋ ሄዶ የግብ ጠባቂው አላዛር የግብ ክልሉን ለቆ መውጣት በማስተዋል የመታው ኳስ መረብ ላይ አርፏል። እየተመሩ የሚገኙት ጅማዎች ግብ ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በአማካያቸው ዳዊት ሌላ ሙከራ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ወጥቶባቸዋል። አጋማሹም በወልቂጤ አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሁለተኛው አጋማሽ ሦስት የአማካይ እና የመስመር አጥቂዎችን ለውጠው ያስገቡት ጅማዎች በጊዜ አቻ የሚሆኑበትን እጅግ ያለቀ አጋጣሚ አምክነዋል። በዚህም በቀኝ መስመር ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው በሙሴ አማካይነት ወደ ሳጥን የላኩትን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ብቻውን ያገኘው መስዑድ ኳስ እና መረብን አገናኘ ተብሎ ሲጠበቅ ተስፋዬ ዳግም የቡድኑ አዳኝ ሆኖ ኳስ መስመሩን እንዳታልፍ አድርጓል።

ጅማ ግብ ለማስቆጠር በመፈለግ ግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱ ከተከላካይ ጀርባ ሰፊ ቦታ እንዲያገኙ የረዳቸው ወልቂጤዎች በ57ኛው ደቂቃ ጫላ ሁለተኛ ግብ ሊያስቆጥርላቸው ነበር። ይህ ተጫዋች በ61ኛው ደቂቃ የጅማ ተከላካይ ኢያሱን በአደገኛ ቦታ ኳስ ተቀብሎ በድጋሚ ክልሉን ለቆ የወጣው አላዛር አናት ላይ በመላክ ኳስ ከመረብ ጋር አዋህዷል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው እየወጣባቸው የሄደው ጅማዎች የተሻለ ኳሱን ቢያንሸራሽሩትም ጎል መድፈር አልቻሉም። በ64ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ምስጋናው ጥሩ ኳስ ልኮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥርም አልቀመስ ያለው ሰዒድ አምክኖበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እዮብ በግራ መስመር እየገፋ የገባውን ኳስ በቀኝ እግሩ ቢመታውም ዒላማውን ስቶ ወጥቶበታል።

ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ መቃኘት የያዙት ወልቂጤዎች በ7ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ከመልስ ውርወራ የተገኘውን ኳስ ጌታነህ ተቀብሎ ተቀይሮ ለገባው ያሬድ ታደሠ ሲሰጠው ፈጣኑ ተጫዋች ኳሱን በግራ እግሩ መጨረሻውን መረብ ላይ አድርጎታል። ከባድ ፈተና ውስጥ የገቡት ጅማዎች በ78ኛው ደቂቃም በዱላ አማካኝነት ሌላ ጥቃት ቢሰነዝሩም የግቡ ቋሚ ለሁለተኛ ጊዜ (ቀድሞ የዳዊትን ኳስ መልሶ ነበር) ግብ እንዲያስቆጥሩ አልፈቀደላቸውም።  ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለው በ84ኛው ደቂቃ ዱላ በተመሳሳይ መስመር በመግባት ወደ መሐል የላከውን ኳስ ዳዊት እስቲፋኖስ ሰዒድ ጀርባ አኑሯታል። ለዚህ ግብ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ወልቂጤዎች በረመዳን ኳስ ጥቃት ቢሰነዝሩም የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ መሐመድኑር ከሳጥን ውጪ ሁለተኛ ግብ ለቡድኑ ቢያስቆጥርም ደቂቃ አልቆ ወደጨዋታው መመለስ ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ቀድሞ በሰበሰባቸው 10 ነጥቦች ሰበታ ከተማን ብቻ በልጦ 15ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።