[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በወልቂጤ ሦስት ለሁለት አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የአሸናፊ እና ተሸናፊ ቡድን አሠልጣኖች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ
ጨዋታው እንዴት ነበር?
“ከባድ ጨዋታ ነበር። ሦስት ነጥቡ እጅግ በጣም ያስፈልገን ነበር። ከወራጅ ቀጠናው ወጥተን ስለዋንጫ ለማሰብ የሚያስችለን ቦታ ላይ ለመቀመጥ የግድ ስለነበር ውጥረት የነበረበት ጨዋታ ነው የተጫወትነው። ለተመልካች ግን አስደሳች ነው ፤ ብዙ ጎል የገባበት ነው።
ቡድንህ በምትፈልገው መንገድ እየመጣ ነው?
“ገና ነው ፤ ይቀረናል። ከባለፈው እንደውም ወረድ ብለን ነው የተገኘነው የሚል ነገር ነው ያለኝ። ምክንያቱም ሦስት ነጥቡ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከራሳችን መንገድ እየወጣን ነበር ስንጫወት የነበረው። ይበልጥ እየሰራን ስንመጣ ግን እናገኘዋለን ብለን እናስባለን።
ረመዳን ስለተጫወተበት መንገድ?
“ለዚህ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የመረጥነው ነገር ነው። ምክንያቱም ጅማዎች ጎል ሲገባባቸው በመስመር የሚፈጥሩት ጫና በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ ይበልጥ እነሱ ላይ ጫና ፈጥረን ለማጥቃት ነው። ለማጥቃት የፈለጉትም የእነሱ ተጫዋቾች ወደመከላከል ስራ ውስጥ እንዲገቡ ነበር ያቀድነው። በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልናል የሚል ዕምነት አለኝ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ላይ ስለተወሰደው የመሐል ሜዳ ብልጫ?
“አዎ ፤ ጅማ ውስጥ ያሉት አማካዮች እንደሚታወቀው በጣም ልምድ አላቸው። የኳስ ክህሎታቸው በጣም ከፍተኛ የሆኑ እና በማሰብ የሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾች ናቸው። እነሱን ከመቆጣጠር የተወሰነ ተቸግረን ነበር። ከዛ ራሳችንን ስናገኝ ጨዋታውን ልንቆጣጠር ችለናል።”
አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር
ወደ ጨዋታው ለመግባት ስለመዘግየቱ..?
“ስህተቶች ነበሩብን፤ ቡድኑ ውጤት ሲያጣ ተጫዋቾቼ ላይ የሚሰማቸው ስሜት አለ። ያንን አስተካክሎ ለመሄድ ዋጋ ከፍለናል። በተጨማሪ በቀላል ስህተቶች ጎሎች ይገቡብን ነበር። እሱን አስተካክሎ ለማነሳሳት ተቸግረን ነበር።
ከተከላካይ ስለሚነጠቁ እና የግብ ጠባቂ አቋቋም ስህተቶች…?
“ዛሬ ትልቁ ችግራችን የኋላ መስመር ነበር። ከዚህ በፊት የምንተማመንበት ቦታ የኋላ መስመሩ ነበር። ዛሬ ግን ለውጤቱ እኔም ኃላፊነት ብወስድም እዛ ቦታ ላይ ችግሮች ነበሩ። ያንን ቦታ የምታናጋው ከሆነ ያበላሽብሃል። ሊያልቅ አካባቢ የተሻሉ የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረናል። ግብ እስካላገባህ ድረስ ግን ዋጋ የለውም። ወልቂጤን እንኳን ደስ አላችሁ ነው ማለት የምችለው።
ስለ ተጋጣሚ ጥንካሬ…?
“ያገኙትን አጋጣሚ ይጠቀማሉ። ፍላጎታቸው ጥሩ ነው። ጨዋታው ሊያልቅ 15 እና 20 ደቂቃ ሲቀረው ግን ተዳክመው ነበር። በዛ አጋጣሚ መጠቀም እንችል ነበር፤ አልተጠቅንበበትም። ዞሮ ዞሮ የየወልቂጤ ጥንካሬው የፊት መስመሩ እና ከኋላ የሚነሱ ተጫዋቾች የቡድኑ ሞተሮች ናቸው።”