[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ማራኪ ያልሆነ እንቅስቃሴ በታየበት ስንታየሁ መንግሥቱ ሳይጠበቅ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻዎች ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት ወደ መሪው ተጠግተዋል።
ወላይታ ድቻ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በጅማ አባ ጅፋር ከተረታበት የጨዋታ ዕለት ስብስብ ሦስት ለውጦችን ያደረገ ሲሆን በዚህም ወንደሰን አሸናፊ ፣ በረከት ወልደዮሀንስ ፣ አዲስ ህንፃ እና ቃልኪዳን ዘላለምን በፅዮን መርዕድ ፣ መልካሙ ቦጋለ ፣ ያሬድ ዳዊት እና እንድሪስ ሰዒድ ተክቶ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ፍሬዘር ካሳ ፣ እያሱ ታምሩ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወጥተው በምትካቸው ኤልያስ አታሮ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና ሀብታሙ ታደሰ ተተክተዋል።
እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀዲያዎች በተነፃፃሪነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም የኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ግብ ዕድል ለመቀየር የነበራቸው ጥረት ውጤታማ ያልነበረ ሲሆን በአጋማሹ በአመዛኙ ከሳጥን ውጭ ከሚደረጉ ሙከራዎች በዘለለ ተጠቃሽ ዕድሎችን ከክፍት ጨዋታ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ለመከላከል ቅድሚያ የሰጡት ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በአንድ አጋጣሚ የሆሳዕና ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ከሰራው ስህተት መነሻነት ለግብ ከቀረቡበት አጋጣሚ ውጪ በመከላከል ከነበራቸው ጥንካሬ ውጪ በማጥቃቱ ይህ ነው የሚባል ሀሳብ አልነበራቸውም።
ነገር ግን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ቀድሞ ለማግኘት ከግቡ የወጣው መሳይ አያኖ የሰራውን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታግዞ ስንታየሁ መንግሥቱ ወላይታ ድቻን ከምንም መሪ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ በመከላከሉ የተጠመዱት ወላይታ ድቻዎች ተጋጣሚያቸው ጥቃት ሊሰነዝርባቸው የሚችላቸውን ክፍት ቦታዎችን እንዳያገኙ ለማድረግ በቁጥር በርከት ብለው ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳሶችን ከመቀባበል ባለፈ አደጋ ለመፍጠር የነበራቸው ጥረት ፍጥነት እንዲሁም ተለዋዋጭነት ይጎድለው ስለነበር ወላይታ ድቻዎችን መፈተን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአጋማሹ በ75ኛው ደቂቃ አበባየሁ ዮሐንስ ከሳጥን ውጭ ከቅጣት ምት የሞከራት እና ፅዮን መርዕድ ያዳነበት ኳስ እንዲሁም ዑመድ ዑኩሪ ያደረገው ሙከራ የሆሳዕና ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወላይታ ድቻዎች ነጥባቸውን ወደ 25 አሳድገው በሰንጠረዡ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ተሸናፊዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በ17 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ዝቅ ብለዋል።