[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ባሳለፍነው ሳምንት ከክለቡ እንዲታገዱ የተደረጉት አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው እና ረዳታቸው እዮብ ማለ በክለቡ አመራር አዲስ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከሊጉ የመውረድ እጣ ፈንታ አጋጥሞት የነበረው ወልቂጤ ከተማ የትግራይ ክልል ክለቦች አለመሳተፋቸውን ተከትሎ በተደረገ የማሟያ ውድድር ዳግም በሊጉ እንዲቆይ ያደረጉት እና ዘንድሮ ከክለቡ ጋር አብረው ቀጥለው የነበሩት አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው እና ረዳታቸው እዮብ ማለ ባሳለፍነው ሳምንት እግድ ተላልፎባቸው አዲስ አሠልጣኝ በቦታው መሾሙ ይታወቃል። “ከሥራዬ ያለአግባብ ነው የታገድኩት” የሚሉት ዋና እና ረዳት አሠልጣኙም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታ አስገብተው የነበረ ሲሆን የክለቡ አመራሮችም በትናንትናው ዕለት ከአሠልጣኞቹ ጋር ፊት ለፊት ወይይት በማድረግ ነበሩ ያሏቸውን የአፈፃፀም እና የዲሲፕሊን ክፍተቶች በማንሳት አዲስ ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ከእነዚህም ክፍተቶች ውስጥ ከሌሎች አሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት አለመኖር ፣ የጨዋታው ሪፖርት እና ግምግማ አለማድረግ ፣ ለሚዲያ ክለቡን የማይመጥኑ አስተያየቶች በመስጠት ፣ ከቴክኒክ ዳይሪክተሩ እና ሌሎች ባለሙያዎች የተሰጡ ቴክኒካዊ ሀሳቦችን በቀናነት አለመቀበል ፣ የክለቡን ሚስጥር አለመጠበቅ ፣ የቅድመ ጨዋታ ስብስባ አለማድረግ ፣ ተጫዋቾችን ለአድማ ማነሳሳት እና በዲስፕሊን አለመምራት እና ሌሎች ነጥቦች ወልቂጤ ከተማ እግርኳስ ክለብ ለዋና አሰልጣኙ በፃፈው ድብዳቤ ላይ ተዘርዝረዋል።
ክለቡ በዚህ መልኩ ያነሳቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ከጠቀሰ በኋላ በድብዳቤው ባሳወቀው ውሳኔ መሰረት አሰልጣኝ ጻውሎስ እና እዮብ ከዛሬ ጀምሮ የወልቂጤ ታዳጊ ቡድንን (B) እንዲያሰሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። በመሆኑም አሠልጣኞቹ ከአስር ቀናት በኋላ የክለቡ ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት ወልቂጤ ከተማ በማቅናት ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ሥራ እንዲጀምሩ ተመላክቷል።