[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች በሁለተኛው የፅሁፋችን ክፍል ተመልክተናቸዋል።
👉 አቤል እንዳለ በመስመር ወይንስ በመሀል ?
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ የጨዋታ ደቂቃን ፍለጋ ቡናማዎቹ ቤት የደረሰው አቤል እንዳለ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የመሰለፍ ዕድልን ቢያገኝም ከአዲሱ ሚናው ጋር ለመላመድ ግን የተቸገረ ይመስላል።
ከጨዋታ ደቂቃ አንፃር የተጠናቀቀውን የጨዋታ ሳምንት ጨምሮ በ9 ጨዋታዎች መሰለፍ የቻለው አቤል በድምሩ ለ658 ደቂቃዎች ያህል ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ከመጫወቻ ቦታ አንፃር ግን በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተ የሚገኝበት ሚና ከዚህ ቀደም ይታወቅበት ከነበረው እና አስደናቂ ብቃቱን በተለይ በደደቢት ቤት ካሳየበት የመጫወቻ ቦታ አንፃር የተለየ ነው።
የአቤል እንዳለ የጨዋታ ባህሪ በመሰረታዊነት ኳስን የሚፈልግ ከመሆኑ አንፃር ይበልጥ ለእንቅስቃሴዎች ቅርብ በሚሆንበት “የነፃ 8” ቁጥር ሚና ይበልጥ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ላይ ወደ ኋላ እየተሳበ ወደ ፊት እየተጠጋ እንዲሁም እንዳሻው ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ እየተሳበ በመንቀሳቀስ መጫወት ይበልጥ ምቾት እንደሚሰጠው የደደቢት ጊዜው ላይ ይታይ ነበር። ከፍታው ላይ ሆኖ ከታየበት ከዚያ ጊዜ በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ ወዲህ ግን ወደ አሰላለፍ ሰብሮ በመግባት በሚፈለገው ደረጃ የእግርኳስ ዕድገቱን ማስቀጠል አለመቻሉን ተከትሎ ነበር በክረምቱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያቀናው። በኢትዮጵያ ቡናም ግን ተጫዋቹ ከአማካይነት ይልቅ ይበልጥ ወደ መስመር ተጠግቶ እንደ መስመር አጥቂነት እንዲጫወት መደረጉ በጨዋታዎች ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲቀንስ እያደረገው ይገኛል።
አቤል በማቀበል (pass) የጨዋታ ሂደቶችን መወሰን የሚፈልግ እንጂ ከመስመር እንደሚነሱ ተጫዋቾች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ተጫዋቾችን ለመቀነስ ከኳስ ጋር በተከላካዮች ላይ የሚሮጥ ተጫዋች አለመሆኑን ተከትሎ በመስመር ላይ ያለው እንቅስቃሴ የቡድን አጋሮቹ ወደ መስመር ተስበው እንዲመጡ በማድረግ ከእነሱ ጋር ከመቀባበል በዘለለ ከመስመር የመነሳቱ ሂደት በአስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር የሚያዋጣ ሙከራ እንዳልሆነ እየተመለከተነው እንገኛለን።
እርግጥ አሰልጣኙ ተጫዋቹን በዚህ ሚና እየተጠቀሙበት የሚገኘው በፍላጎት ወይንስ ስብስባቸው ውስጥ ካለው የስብስብ ጥልቀት ችግር ነው የሚለው መልስ የሚሻ ሲሆን ተጫዋቹ ግን በዚህ ሚና በቀደመው ልክ አገልግሎት እየሰጠ ስላለመሆኑ ግን መናገር ይቻላል።
👉 ተስፋ የሚጣልበት ገዛኸኝ ደሳለኝ
ወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና የመሀል ተከላካይ ገዛኸኝ ደሳለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ በቀዳሚ ተሰላፊነት በታየበት ጠንካራው መርሐግብር ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል።
የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ በቅድመ ውድድር ዘመን ባሳየው እንቅስቃሴ መነሻነት የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የአሰልጣኝ ቡድን በማሳመን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ደሳለኝ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መልካም የሚባልን እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።
በሊጉ በእስካሁኑ ጉዞ በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ተቀይሮ በመግባት ስድስት ያህል ደቂቃዎችን ብቻ በሜዳ ላይ ተሰልፎ የተጫወተው ደሳለኝ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ጥያቄ ሲነሳበት የቆየው ቴዎድሮስ በቀለን በመተካት እጅግ ወሳኝ በነበረው የፋሲል ከነማው ጨዋታ በቡድኑ ቀዳሚ ተሰለፊነት ተካቶ ተመልክተነዋል። በዚህም ከጨዋታው ክብደትም ሆነ ከዕድሜው አንፃር ሊቸገር ይችላል የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም ጥሩ የሚባል የጨዋታ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል።
እርጋታን የተላበሰው ወጣቱ ተከላካይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው አፈፃፀምም ሆነ ኳሶችን በአጭርም ሆነ በረጅም ለማሰራጨት ያለው ዝግጁነት እንዲሁም ንቃቱ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። በጨዋታው የነበረውን እንቅስቃሴ ለተመለከት በሊጉ ረዘም ላለ ጊዜ የመጫወት ልምድ ያለው እንጂ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ አይመስልም ነበር።
ተፈጥሯዊ የግራ እግር የመሀል ተከላካዮች እጥረት ባለበት እግር ኳሳችን እንደ ደሳለኝ ያሉ አስፈላጊውን እግርኳሳዊ ክህሎትን ያሟሉ ይበልጥ የመሻሻል አቅም ያላቸው ተጫዋቾች መምጣት ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን ተጫዋቹ በአድናቆቶች ሳይዘነጋ ራሱን በትልቅ ደረጃ ለማሳየት አንገቱን ደፍቶ መስራት እንዳለበት ግን መረሳት የለበትም።
👉 ለሰበታ ማጥቃት ተስፋን የፈነጠቀው ዱሬሳ ሹቢሳ
14ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው ውድድር በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በመለያየት አሳክተዋል።
ከወትሮው በተለየ በህብረት ለመከላከል እና ለማጥቃት ይሞክር በነበረው የሰበታ ከተማ ስብስብ ውስጥ የመስመር ተጫዋቹ ዱሬሳ ሹቢሳ አበርክቶ እጅግ የላቀ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ከባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ቅብብል ስህተት ካስቆጠረው ግብ በተጨማሪ በአጋማሹ ሰበታ ከተማዎች የፈጠሯቸው ሁሉም የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እሱ ከተሰለፈበት የግራ መስመር መነሻቸውን ያደረጉ ነበሩ።
ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ የነበሩ ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ከአምናው መነሻነት ይበልጥ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ተጫዋቾቹ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስብስብ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችል ቆይቷል።
በባህር ዳሩ ጨዋታ ምንም እንኳን ዱሬሳ በመስመር ተጫዋችነት ቢሰለፍም ይበልጥ ወደ ውስጥ አጥብቦ እንደ “Inverted Winger” ሲጫወት የነበረ ሲሆን ከኳስ ውጪም በነበረው እንቅስቃሴ በጣም አጥቦ ሲንቀሳቀስ ይታይ ነበር። በዚህም ዱሬሳ በተቃራኒ አቅጣጫ የተሰለፈው ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ኋላ ተስቦ ይበልጥ ወደ መሀል ይገባ ስለነበር በተጋጣሚ ሳጥን በሚያጠቁበት ወቅት በቁጥር እንዳያንሱ ለአጥቂው ኒስባምቢን ተጠግቶ ሲጫወት ተመልክተናል።
በዚህ ረገድ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ዱሬሳ ድንቅ የመጀመሪያ አጋማሽ ቢያሳልፍም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ፍፁም ተቀዛቅዞ ተመልከተነዋል። ይህን ሂደት በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመጀመሪያ ተመራጭነት በጀመረባቸው ጨዋታዎችም የተመለከትን ሲሆን ምናልባት ተጫዋቹ ጉልበቱን በአግባቡ ከመጠበቀም አንፃር ውስንነቶች እንዳሉበት የሚያሳይ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ትልቅ ተጫዋችነት ለመቀየር በዚህ ረገድ ራሱን ይበልጥ ማሻሻል እንደሚኖርበት የጠቆመ ነበር።
የሆነው ሆኖ ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያሳየው ብቃቱ ሰበታ ባለፉት ጨዋታዎች ያጣውን ነገር በደንብ ያሳየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ጨዋታዎች ቡድኑ ተጫዋቹን ይበልጥ ሊጠቀምበት እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር።
👉 ጋናዊያን በበዛት እና ትኩረት በመሳብ የታዩበት ጨዋታ
በድራማዊ ክስተቶች የታጀበው እና ሀዋሳ ከተማን ከመከላከያ ያገናኘው ጨዋታ አምስት ጋናውያንን በአንድ ጨዋታ ያስመለከተንን አጋጣሚ ፈጥሮ አልፏል።
በጨዋታው በሀዋሳ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ እና የመሀል ተከላካዩ ላውረስ ላርቴን የተመለከትን ሲሆን በተጋጣሚያቸው መከላከያ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ ፣ በጨዋታው የሚና ለውጥ አድርጎ በመሀል ተከላካይነት የተሰለፈው ኢማኑኤል ላርያ እና አጥቂው ኡኩቱ ኢማኑኤልን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ተሰልፈው ሲጫወቱ ተመልክተናል።
ታድያ እነዚሁ አምስት ተጫዋቾች በጨዋታው ሂደት ወሳኝ በነበሩ ክስተቶች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ። የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሙንታሪ መከላከያን አቻ ያደረገችው ሁለተኛ ግብ ስትቆጠር ስህተት ሲሰራ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ደግሞ የቢኒያም በላይን ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ቡድኑን ታድጓል። ሌላኛው የቡድን አጋሩ የሆነው ላውረንስ ላርቴ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ በረጅሙ የተጣለን ኳስ ሆን ብሎ በእጅ በመንካቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በመከላከያዎች በኩል ኡኩቱ ኢማኑኤል አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ግብን ሲያስቆጥር ኢማኑኤል ላርያ ደግሞ አጨቃጫቂ በነበረ ሂደት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለተኛዋን የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ኳሷን በእጁ የነካ ሲሆን ግብ ጠባቂው ክሊመንት ቦዬም እንዲሁ በመጨረሻ ደቂቃ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ማዳን ችሏል።
በሊጋችን ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እያሽቆለቆለ የሚገኙት የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን በተመለከተ በቅርብ ጊዜያት ከተመለከተናቸው ጨዋታዎች የሀዋሳ እና መከላከያ ፍልሚያ በቁጥር በርከት ያሉ የአንድ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን የተመለከትንበት ጨዋታ ሊሆን ይችላል።
👉 ድንቅ ቀን ያሳለፈው ኡቸና ማርቲን
ናይጄሪያዊው የአርባምንጭ ከተማ ተከላካይ ኡቸና ማርቲን ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ በማስቻሉ ረገድ የተወጣው ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።
በስድስት ጨዋታዎች ለ439 ያህል ደቂቃዎች መጫወት የቻለው ግዙፉ ናይጄሪያዊ ተከላካይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተከላካይ ጀርባ በረጃጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት የሚፈልገው የቅዱስ ጊዮርጊስን የማጥቃት ፍላጎት በማክሸፍ ረገድ ቁልፍ ሚና ነበረው።
በተለይ ደግሞ ከላይ በጠቀስነው የቅዱስ ጊዮርጊሶች የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚወጣው እስማኤል ኦሮ-አጎሮን እንቅስቃሴ በንቃት በመከታተል ያቋርጥ የነበረበት መንገድ የተለየ ነበር። በአንድ ለአንድ የአየር ላይ ግንኙነቶች በተወሰነ መልኩ ጉልበትን ቀላቅሎ ይጫወት የነበረው ተከላካዩ በተደጋጋሚ ኦሮ-አጎሮ ላይ ብልጫ ሲወስድ የተመለከትን ሲሆን በጨዋታውም ተጫዋቹ የአርባምንጭ የጨዋታ መንገድ የሚፈልገው ትክክለኛ ሰው ስለመሆኑ ዳግም ማረጋገጫ የሰጠበት ነበር።
ለመጨረሻ ጊዜ በ7ኛው ሳምንት አርባምንጭ ጅማ አባ ጅፋርን ገጥሞ ያለ ግብ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ዳግም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የተመለሰው ኡቸና በሁለቱ ተከታታይ ጨዋታዎች ያሳየው አስደናቂ ብቃት ተጫዋቹ በሁለተኛው ዙር ውድድር የቡድኑ ሁነኛ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።
👉 የተባረክ ሄፋሞ ድርጊት…
ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 3-2 በረታበት ጨዋታ መነጋገርያ ከነበሩ ክስተቶች አንዱ የነበረው በ80ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወጣቱ አጥቂ ተባረክ ሂፋሞ የፈፀመው ያልተገባ ድርጊት ነበር።
ተጫዋቹ በ88ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሀዋሳዎች ወደ መከላከያ የማጥቃት ወረዳ ያደረሱትን ኳስ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ እያጠበበ ከገባ በኋላ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ የመከላከያው አምበል አሌክስ ተሰማ በእጅ በመንካቱ የተነሳ ሀዋሳዎች በጨዋታው አምስተኛ የነበረችውን የፍፁም ቅጣት ምት አስገኝቷል ፤ አነጋጋሪው ክስተት የተፈጠረው ከዚህ በኃላ ነበር።
ወጣቱ አጥቂ ገና ውሳኔው እንደተሰጠ በፍጥነት የፍፁም ቅጣት ምቱን ለመምታት ወደ ቡድን አጋሮቹ እየሮጠ ቢሄድም ፍፁም ቅጣት ምቱን የመምታት ኃላፊነትን ግን የቡድኑ ተቀዳሚ መቺ የሆነው አምበላቸው ዓዲስዓለም ተስፋዬ ኃላፊነቱን መውሰዱን ተከትሎ ተባረክ በግልፅ በሚታይ መልኩ በተደጋጋሚ ብስጭቱን ሲገልፅ ተመልከተናል። በዚህ ያላበቃው ተጫዋቹ የቡድን አጋሮቹ ሊያረጋጉት ሲሞክሩም እንዲሁ በብስጭት እጆቹን ሲያወራጭ ታይቷል።
እርግጥ አጥቂ ተጫዋቾች ግቦችን ለማስቆጠር ያላቸው አልጠግብ ባይነት ተፈላጊ የአጥቂ ተጫዋቾች ባህሪ እንደሆነ ቢታመንም በቡድን አሰልጣኞች ሆነ ተጫዋቾች ለሚሰጡ ትዕዛዞች ተገዢ መሆን ግን የግድ ይላል። ተባረክ ምንም እንኳን የመጀመሪያውን የፕሪሚየር ሊጉን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት የነበረው ቢሆንም እጅግ ተለዋዋጭ የነበረ ይዘት በነበረው ጨዋታ ምናልባት ተቆጥራ ብትሆን ቡድኑን ይበልጥ ልታረጋጋ ትችል የነበረችውን የፍፁም ቅጣት ምት በቡድኑ የተሻለ የፍፁም ቅጣት ምቶች የማስቆጠር ንፃሬ ላለው ተቀዳሚ መቺ በመሰጠቱ ከግል ስሜቱ ወጥቶ ይበልጥ እንደ ቡድን ማሰብ በተገባው ነበር።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ዘርዓይ ሙሉ ተከታዩን ሀሳብ በጉዳዩ ዙርያ ሰጥተዋል።
“የመጀመርያ መቺ አዲስዓለም ነው። ብሩክ አጥቂ ስለሆነ እርሱ እንዲመታ ፈቅዶለት ነው ፤ ሁለተኛ መቺ እርሱ ነው። ተባረክ ያደረገው ነገር ትልቅ ስህተት ነው ፤ እርሱ መቺ አይደለም ፤ ምርጫችንም አይደለም። እርሱ መጠየቅ በሚገባን መጠን እንጠይቃለን። ዞሮ ዞሮ እርሱም ስሜት ነው ጎል አላገባም ጎል አግብቶ ወደ ጎል አግቢነት ለመግባት ነው። ተጫዋቾቹም እርሱ እንዲመታ ፈልገው ነበር። ለኔ ግን የመጀመርያ መቺያችን ዓዲስዓለም ነው ፤ እርሱም ስቷል ይሄን እናስተካክላለን። ያው እንዳንዴ ይፈቃቀዳሉ አንዱ አንዱ እንዲመታ ይህ የቡድኑን መንፈስ ያሳያል ፤ ይህ በቀላሉ የሚስተካከል ነው።”