የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 11ኛ ሳምንት ሲጠቃለል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 11ኛ ሳምንት ትናንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች የተደረገ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ መሪነት ፣ ቡራዩ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድል አስመዝግበዋል። ነቀምቴ ነጥብ ሲጥል ኢትዮጵያ መድን ልዩነቱን ያጠበበበትን ወሳኝ ድል አሳክቷል።

ምድብ ሀ

በዐፄ ቴዎድሮስ የሚደረገው ጨዋታ በዚህ ሳምንት ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተዛወረ ሲሆን ሁሉም የዚህ ሳምንት ጨዋታዎችም ተካሂደውበታል። ትናንት ሻሸመኔን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት 2-1 ተጠናቋል። በጨዋታው በ4ኛው ደቂቃ የሻሸመኔው የፊት መስመር ተጫዋች አብዲ ሁሴን ባስቆጠራት ግብ ቡድኑ መምራት ቢችልም ለንግድ ባንክ ከሪም መሀመድ ባስቆጠራት ግብ አቻ በመሆን ወደ እረፍት አምርተዋል። ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች በአዳም አባስ የማሸነፊዎያን ግብ አስቆጥረዋል። በሁለተኛው ዙር መሻሻል ያሳየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከታታይ ያሳከውን ድል ተከትሎ መሪዎቹ ላይ መጠጋት ችሏል።

በ8:00 ላይ አምቦ ከተማ ከ ገላን ያደረገት ጨዋታ በርካታ ግብ ያስመለከተ ሆኖ አልፎል። በገላን 4-2 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታው የፊት መስመር ተጫዋቹ ጫላ ከበደ አምቦን ቀዳሚ ቢያደርግም በግማሽ ዓመቱ ገላንን የተቀላቀለው የኋላሸት ፍቃዱ ቡድኑን አቻ አድርጓል ። ከእረፍት መልስ ገላን ከተማዋች በበኃይሉ ወገኔ፣ አረጋኸኝ ማሩ እና ፍርድአወቅ ሲሳይ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ አድርገዋል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አምቦን ከሽንፈት ያላዳነች ኳስ ግዛቸው ኃይሉ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ጨዋታው በገላን ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ10:00 የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ጌዴኦ ዲላ እና ከመሪዎቹ እየራቀ የሚገኘው ጋሞ ጨንቻን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የምድቡ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ አንደኛ ደረጃ ላይ በነበረው ነገሌ አርሲ እና በተከታይ ደረጃ ተቀምጦ በነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ በከፍተኛ ፉክክር እና ውጥረት ታጅቦ በኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተገባዷል። ያለ ጎል የመጀመርያውን አጋማሽ በተገባደደው ጨዋታ ከእረፍት መልስ ከፍተኛ ግለት የታየበት ሲሆን በ64ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። ጎሉ የተቆጠረበት ሂደት ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል በነገሌ አርሲዎች በኩል ተቃውሞ የቀረበ ሲሆን ክስ አስመዝግበው ጨዋታው ቀጥሏል።

የምድቡ መሪነታቸውን መልሰው ላለመነጠቅ ትግል ያደረጉት ነገሌዎች በ78ኛው ደቂቃ ከርቀት የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ምስጋናው ግርማ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሲመታው በግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ቢመለስበትም መልሶ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ አቻ መሆን ችለው ነበር። ጨዋታው በዚሁ ውጤት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ተቀይሮ በገባው ፀጋ ደርቤ አማካኝነት አስቆጥረው ወሳኝ ድል አሳክተው ወጥተዋል። ውጤቱን ተከትሎም ባለፈው ሳምንት ሽነፈት በማስተናገዱ መሪነቱን ለነጌሌ አርሲ አስረክቦ የነበረው ኤሌክትሪክ ወደ ቦታው ተመልሷል።

ምድብ ለ

በባቱ ሼር ሜዳ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ጨዋታዎች ቡራዩ ከተማ ወደ ድል ሲመለስ ቡታጅራ ከተማም ወደ መሪዎቹ ጎራ ጠጋ ያለበትን ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

ሐሙስ በ4:00 ላይ ካፋ ቡና እና ሰንዳፋ በኬን ያገናኘው ጨዋታ ረጅም ደቂቃ ያለምንም ግብ ዘልቆ ለከፋ ቡና በ79ኛው ደቂቃ ዳዊት ታደሰ ቢያስቆጥርም ሰንዳፋ በኬዎች በ82ኛው ደቂቃ ዳኛቸው ብርሃኑ ባስቆጠረው ጎል አቻ ወጥተዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲን ከስልጤ ወራቤ ያገናኘው የ8፡00 ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። በተከታታይ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ለገጣፎ ለገዳዲም ከመሪው ቡራዩ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ሦስት ሆኗል።

በዘንድሮው ውድድር ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ የተመለሰው ቡራዩ ከተማ የምድቡ መሪነትን ያጠናከረበትን ውጤት በኮልፌ ላይ አስመዝግቧል። በቡራዩ 3-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ መለሰ ኒሻሙ እና ጴጥሮስ ገዛኸኝ አስቆረዋል። ድሉን ተከትሎ በመጣበት ዓመት ድንቅ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው ቡራዩ ነጥቡን 24 አድርሶ መሪነቱን እንዲያጠናክር ረድቶታል።

በዘሬው ዕለት የመድቡ ጨዋታዎች ቀጥለው 8፡00 ቤንች ማጂ ቡና ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ 1-1 ተለያይተዋል። የፊት መስመር ተጫዋቹ ወንድምአገኝ ኬራ የቤንቺ ማጂ ቡናን ግብ ሲያስቆጥር በረከት አድማሱ በራሱ ላይ ባስገባው ግብ ቂርቆስ አቻ መሆን ችሏል።

በምድቡ የሳምነቱ የመጨረሻ ጨዋታ ከአሰልጣኝ መሳይ ጋር የተለያያው ቡታጅራ ከተማ ሺንሺቾን 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ለፈረሰኞቹ እንዳለማው ታደሰ በ32ኛ እና 34ኛ ደቂቃ ሲያስቆጥር ሺንሺቾን ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ግብ ዘላለም ፍቃዱ አስቆጥሯል።

ምድብ ሐ

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ሐ ውድድር በዚህ ሳምንት በመሪዎች ትንቅንቅ ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በትናንት ጨዋታዎች ረፋድ 4፡00 ላይ ሶዶ ከተማን የገጠመው መሪው ነቀምቴ ከተማ በወራጅ ቀጠና ከሚገኘው ሶዶ ጠንካራ ፉክክር ገጥሞት ጨዋታውን ያለ ጎል አጠናቋል። ውጤቱም ነቀምቴ ከተከታዩ መድን ያለውን ልዩነት እንዲያጠብ አስገድዶታል።

8፡00 ላይ የአሠልጣኝ ለውጥ ያደረገው ሀምበሪቾ ዱራሜ ፌዴራል ፖሊስን በልዑልሰገድ አስፋው ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። 10፡00 ላይም በተመሳሳይ አቃቂ ቃሊቲ ዘንድሮ መጥፎ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የካ ክፍለከተማን ገጥሞ በአዳነ ተካ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የምድቡ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ተከታታይ ውጤቶች ያንሰራራው ጉለሌ ክ/ከተማ በአንድ ነጥብ ከሚያንሰው ደቡብ ፖሊስ ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ ተገባዷል። የመጀመሪያውን አጋማሽ ግብ ሳይስተናግድ ቢጠናቀቅም ከዕረፍት መልስ ሄኖክ ሙሌ በ51ኛው ደቂቃ ላይ ጉለሌን መሪ መሪ ሲያደርግ ብዙም ሳይቆይ በ65ኛው ደቂቃ ዮናስ ወልዴ ደቡብ ፖሊስን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የምድቡ የመጨረሻ የሳምንቱ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን እና ጅማ አባ ቡና የተከናወነ ሲሆን ትናንት መሪው ነቀምቴ ከተማ ከወላይታ ሶዶ ባደረገው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ልዩነቱ ይጠባል ዌይስ ባለበት ይዘልቃል የሚለው ተጠባቂ አድርጎት ነበር። ጨዋታው በመድን 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ቢንያም ካሳሁን የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዶ በጭማሪ ሰዓት (45+2) እና ከዕረፍት መልስ ሀይከን ደዋሙ ጎሎቹን አስኦጥረዋል። ድሉም ከመሪው ነቀምቴ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ እንዲያጠብ አስችሎታል።