የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ተጀምሯል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ2014 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በጎንደር ዐፄ ፋሲ ደስ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል።

ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲጀመር የምድብ ሀ ውድድር በደማቅ ሁኔታ በጎንደር ከተማ በሲዳማ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ተከፍቷል። ውድድሩን የጎንደር ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ንግግር በማድረግ ከፍተውታል። በዕለቱ በክብር እንግድነት ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለን ጨምሮ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኢብራሂም አህመድ፣ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳይያስ ታፈሰ፣ የዳኞች ልማት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ፣ የጎ/ከ/አስ/ር ባ/ቱ/ወ/ስፖርት መምሪያ ም/ኃላፊ ኢንስትራክተር ካሳሁን ምንተስኖት እና የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን አባላት የተገኙበት ሲሆን የከተማ አስተዳደሩም ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት ታዳጊዎችን ኤርፖርት ድረስ በመሄድ አቀባበል አድርጓል።

ሲዳማ ከተማ 1 – 0 አዳማ ከተማ

የእለቱ የክብር እንግዶች ባስጀመሩት ጨዋታ ተመጣጣኝ የሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ያደረጉት በሁለቱ ቡድኖች ብዙም ማራኪ ባልነበረው ጨዋታ መሐል ሜዳ ልይ ብልጫ ለማድረግ ሲደረጉ የነበሩ ፉክክሮች እና ያልተሳኩ የኳስ ቅብብሎች የበዙባቸው የነበሩ ሲሆን ከእረፍት መልስ ግን ሲዳማዎች ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ሲዳማዎች በተሻለ ወደግብ ቢደርሱም ወደ አስደንጋጭ የግብ እድልነት በመቀየሩ ረገድ ግን ስኬታማ አልነበሩም።

ጨዋታው በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ በሚመስልበት እንቅስቃሴ መሐል በፍቅሩ ግዛቸው በ78ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ በጭንቅላቱ በመግጨት ሲደማ ቡናን አሸናፊ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5 -0 ሀላባ ከተማ

ኤሌክትሪክ ሀላባ ላይ የጎል ዝናብ ባዘነበት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ አለመሆን ታይቶባቸዋል። ፍፁም የበላይነት ወስደው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች በ20ኛው ደቂቃ በናሆም ተስፋዬ ግሩም ቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉ ሲሆን ጥሩ የመሐል ሜዳ ብልጫ የነበራቸው ኤሉክትሪኮች ጨዋታውን በፈለጉት መልኩ ሲከውኑ አስተውለናል። በ40ኛው ደቂቃ ላይም ናሆም ተስፋዬ ወደ ሳጥን በግራ ሳጥን ጠርዝ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ቀኝ መስመር ለአብዱል መጅድ ሁሴን አቀብሎት አብዱል መጅድ ወደ ግብ ቀይሮት ሁለት ለዜሮ እየመሩ ወደ እረፍት ወጥተዋል ።

ከእረፍት መልስም በነበሩበት የጨዋታ ፍላጎት የተመለሱት ኤሌክትሪኮች በ52ኛው ደቂቃ ላይ ናሆም ተስፋዬ ሳጥን ውስጥ በመገኘት ወደግብ የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ጥሩ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። ሆኖም ተጨማሪ ግብ ለማግበት 5 ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው ሲሆን ግብ ጠባቂው ከርቀት የተመታበትን ኳስ ይዞ ሲለቀው ዳዊት ሲሳይ ወደግብ የቀየረው ሲሆን ከዛ በኋላ ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ላይ ከመዓዘን የተሻማን ኳስ ሳልዓዲን ካሚል ወደ ግብ በመቀየር ለቡድኑ አራተኛ ግብ አስቆጥሯል። በጨዋታው መጠናቀቂያ በድጋሚ የተነቃቁት ኤልፓዎች 90ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ታደሰ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 5-0 የተጠናቀቀ ሲሆን በውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ከሳጥን ውጭ ድንቅ ግብ ላስቆጠረው ኤፍሬም ታደሰ የኳስ ሽልማት አበርክቷል።

በጨዋታው ላይ የኤሌክትሪኩ የአጥቂ አማካይ ናሆም ተስፋዬ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል ።

አርባምንጭ ከተማ 3 -1 ሰበታ ከተማ

ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እንዲሁም የአርባምንጭ ረጃጅም ኳሶች እና ፈጣን አጥቂዎች ችሎታ ጥሩ በነበረበት ጨዋታ ሰበታ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በ29ኛው ደቂቃ ጌታሁን ዳዲ ራሱ ላይ ያስቆጠረው ግብ አርባምንጭን ቀዳሚ ያደረገ ሲሆን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጥሩ መነቃቃት ያደረጉት አርባምንጮች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ችለው ነበር። በርካታ ኳሶች ከጨዋታ ውጭ እየተባሉባቸው የነበረ ቢሆንም ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይቷል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማ ኪሩቤል ንጉሴ ከ ሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት በሰበታ በኩል እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር ።

41ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከመሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ አብዬ ደለለው ይዞ ገብቶ ያስቆጠረው ግብ ለአርባምንጭ ከተማ ሁለተኛ ሆኗል። በድጋሜ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዬ ደለለው የተሻገረለትን ኳስ አስቻለው ስሜ ወደግብ ቀይሮ ቡድኑ 3ለ0 እየመራ ወደ እረፍት አምርቷል።

ከእረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ በአርባምንጭ በኩል ያሬድ መኮንን ከዮርዳኖስ እያሱ ጋር በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ደርሰው ያሬድ መኮንን የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው የመለሰበት በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀስ ኳስ ነበር። ከስድስት ደቂቃ በኋላ ሰበታ ቦጃ ጊዴቻ ግሩም የቅጣት ምት ያስቆጠረ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይታይት በአርባምንጭ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአርባምንጭ ከነማ በኩል ቦጃ ጊዴቻ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን በአርባምንጭ በኩል አቢዬ ደለለው ጥሩ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን ተመልክተናል ።

በአሰላ ከተማ ሊካሄድ የነበረው የምድብ ለ ውድድር በጣለው ከፍተና ዝናብ ምክንያት ሜዳው የማጫወት ደረጃ ላይ ባለመገኘቱ ሳይከናወን ቀርቷል።