ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ሉሙምባሺ ይገኛል፡፡ ፈረሰኞቹ ከባህርዳር መልስ ማክሰኞ እና ረቡእ ልምምድ በማድረግ ሀሙስ ጠዋት ወደ ስፍራው የተጓዙ ሲሆን አሰልጣኝ ማርት ኑይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በባህርዳር የሰሩትን መድገም እንደሚገባው በመጨረሻው ልምምድ ላይ ከተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ተናግረዋል፡፡
“ባህርዳር ላይ የሰራነውን በሉቡምባሺም ደግመን ማሳየት አለብን፡፡ በእሁዱ ጨዋታ ጠንካራ ፈተና እንደምንፈጥርባቸው አስባለው፡፡ ከዛ ውጤቱን መጠብቅ ይኖርብናል፡፡” ብለዋል፡፡ የቲፒ ማዜምቤ ሜዳ የሆነው ስታድ ዱ ቲፒ ማዜምቤ የመጫወቻ ሜዳው የሰው ሰራሽ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰው ሰራሸ ሽሜዳ በሆነው አበበ ቢቂላ ልምምድ ያልሰሩበትን ምክንያት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ያብራራሉ፡፡ “እውነት ለመናገር ዝግጅታችን የሚጀምረው ሉቡምባሺ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም እስከ ቅዳሜ ድረስ ጨዋታውን በምናደርግበት የሰው ሰራሽ ሳር በተነጠፈበት ሜዳ ላይ ነው ልምምድ የምንሰራው፡፡ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምድ ያልሰራንበት ምክንያት የስታደ ቲፒ ማዜምቤ እና የአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሰውሰራሽ ሳር ንጣፍ ስለሚለያይ ነው፡፡ ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቲፒ ማዜምቤ የሚያደርጉት ጨዋታ እሁድ 10:30 ላይ ሲካሄድ ፈረሰኞቹ ካሸነፉ አልያም ከ2 ግብ በላይ በሆነ አቻ ውጤት ከተለያዩ ወደ 2ኛው ዙር ያልፋሉ፡፡