[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ14ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ምርጥ ብቃት አሳይተዋል ብለን የመረጥናቸው ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው።
የተጫዋች አደራደር ቅርፅ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
አቤል ማሞ – ኢትዮጵያ ቡና
በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለ1019 ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡናን ግብ የጠበቀው አቤል ባሳለፍነው ሳምንት ለአድናቆት የሚዳርገው እንቅስቃሴ በግብ ብረቶቹ መሐል በመቆም አሳልፏል። በጨዋታ ሳምንቱ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያድኑ የተመለከትናቸው ግብ ጠባቂዎች ቢኖሩም አቤል ወደግብነት ለመቀየር ከፍተኛ ዕድል የነበራቸው ሦስት ኳሶችን ያዳነበት መንገድ ከተፎካካሪዎቹ የተሻለ ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎት ቦታውን አግኝቷል።
ተከላካዮች
ተስፋዬ ነጋሽ – ወልቂጤ ከተማ
ሰራተኞቹ ጅማ ላይ ድል ሲቀዳጁ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተስፋዬ ብቃት እጅግ ጥሩ ነበር። እንደ ዘመናዊ የመስመር ተከላካዮች በሦስተኛው የሜዳ ሲሶ የመገኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ተጫዋቹ ካልተጠበቀ ቦታ የቡድኑን የመክፈቻ ጎል ከማስቆጠሩ ባለፈ የተጫዋች ጀርባ ሩጫዎችን እያረገ የመጨረሻ ኳሶችን ለማመቻቸት አልፎም ራሱ ለማስቆጠር የሚጥርበት መንገድ የሚደነቅ ነበር። ዋነኛ ሀላፊነቱ የሆነው መከላከልንም በጥሩ ሁኔታ ሲከውን የነበረ ሲሆን በተለይ በ48ተኛው ደቂቃ ቡድኑን በጨዋታው ያቆየች ኳስ ከግቡ መስመር እንዳታልፍ ማረጉ በጨዋታው የጎላ ተፅዕኖ እንዲኖረው አስችሏል።
ኡቸና ማርቲን – አርባምንጭ ከተማ
ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የመግባት ዕድል ያገኘው ናይጄሪያዊው ተከላካይ በከባዱ ጨዋታ ቡድኑ እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተለይ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኦሮ-አጎሮ ከተሻጋሪ ኳሶች ግብ እንዳያገኝ ሲታትር ነበር። ከዚህ ውጪ ሀይል የተቀላቀለበት አጨዋወት በመከተል ለጊዮርጊስ ተጫዋቾች ምቾት በመንፈግ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎችን እንዳይሞክሩ ታትሯል።
ገዛኸኝ ደሳለኝ – ኢትዮጵያ ቡና
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የነጠ ብቃት ያሳዩ የመሐል ተከላካዮች ባይኖሩም ወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች በአንፃራዊነት ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ከፋሲሉ ጨዋታ በፊት በሊጉ 6 ደቂቃዎችን ብቻ የተጫወተው ገዛኸኝ እጅግ ልምድ እና እርጋታ በሚፈልገው ቦታ ላይ ሳይሸበር ያደረገው እንቅስቃሴ ከእድሜው በላይ እንደበሰለ የሚጠቁም ነበር። በመሬት እና አየር የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ በቀላሉ እጅ የማይሰጠው ተጫዋቹንም በምርጥ ቡድናችን ከኡቸና ማርቲን ጎን እንዲቆም አድርገነዋል።
ረመዳን የሱፍ – ወልቂጤ ከተማ
በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና ስር የተመቸው የሚመስለው ረመዳን ባሳለፍነው ሳምንት በምርጥ ቡድናችን በተጠባባቂነት ቢያዝም በዚህኛው ሳምንት ያሳየው ብቃት ግን 11 ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። የግራ መስመሩም ከጫፍ እስከ ጫፍ ሲሮጥበት የነበረው ረመዳን የአማካይ እና የመስመር አጥቂዎቹ አጥበው ስለሚጫወቱ ለቡድኑ ስፋት ለመስጠት ወደፊት ተጠግቶ ሲጫወት ነበር። ጅማዎችም እርሱ በተሰለፈበት መስመር በተቃራኒው ያስገቧቸውን የመስመር ተከላካይ እና አጥቂ ገና በአጋማሹ እንዲቀይሩ ያደረጋቸው አንድም የእርሱ ብቃት ነበር።
አማካዮች
ዳዊት እስጢፋኖስ – ጅማ አባ ጅፋር
ጥሩ ብቃት ያሳዩ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በታዩበት የጅማ እና ወልቂጤ ጨዋታ በአማካይ መስመር ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ዳዊት እስጢፋኖስ አንደኛው ነው። ለተጋጣሚ ሳጥን እጅግ ተጠግቶ እንዲንቀሳቀስ የተደረገው ተጫዋቹ በጨዋታው አንድ ጎል ብቻ ቢያስቆጥርም በመስመሮች መካከል እየተገኘ የፈጠራቸው ሁለት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ልዩነት ለመፍጠር የተቃረቡ ነበሩ።
በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ
በዛብህ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኳስ እና መረብን በማገናኘት የቡድኑ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነበትን ጨዋታ አሳልፏል። አይደክሜው አማካይ ከራሱ ሜዳ የሚነሳውን የቡድኑን የኳስ ቅብብሎሽ እንድገት እንዲኖረው እያረገ በመጨረሻው የሜዳ ክልል ለግብ ማስቆጠሪያ ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ሲጥር የሚስተዋል ሲሆን ዘግየት ያሉ ሩጫዎችንም እያደረገ በተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ ይገኛል። በቡናውም ጨዋታ ይህ በጉልህ ታይቷል።
ዘካሪያስ ከበደ – አዳማ ከተማ
በዘንድሮ የውድድር ዘመን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት ለመጀመሪያ ጊዜ ለአዳማ ግልጋሎት የሰጠው ዘካሪያስ (አንድ ጊዜ ተቀይሮ በመግባት መጫወቱ ልብ ይሏል) ሳይጠበቅ ጥሩ ቀን አሳልፏል። ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ለቡድኑ ጥንካሬ ሲሰጥ የነበረው ተጫዋቹ ልኬታቸው ጥሩ የሆኑ የአግድሞሽ ኳሶችን ለሁለቱ የመስመር ተመላላሾች እንዲሁም ለፈጣኖቹ አጥቂዎች ከተካላካይ ጀርባ ሲልክ አስተውለናል። የዳዋ ግብ ስትቆጠርም የእርሱ ረጅም ኳስ ዋጋዋ ከፍ ያለ ነበር።
አጥቂዎች
ጫላ ተሺታ – ወልቂጤ ከተማ
ከጌታነህ በመቀጠል የወልቂጤ የግብ ምንጭ የሆነው ጫላ ባሳለፍነው ሳምንት ሦስተኛ ግቡን አስቆጥሯል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ በመስመሮች እና በተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ጀርባ እየተገኘ ቦታዎችን ለመጠቀም ሲጥር ይታያል። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ከወትሮ በተለየ የመታተር ባህሪ እየታየበት ኳሶችን ለመንጠቅ ሲሞክር ነበር። በጨዋታው የመጨረሻውን ሩብ ሰዓት ባይጫወትም የተጋጣሚን ተጫዋቾች እንዲሳሳቱ ለማድረግ ሲያደርግ የነበረው ጥረት በግብ በመታጀቡ በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል።
ዳዋ ሁቴሳ – አዳማ ከተማ
ከቅጣት መልስ ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ የረዳው ዳዋ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል። ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሁለቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው (በማስቆጠር እና አሲስት በማድረግ) ዳዋ ለድሬዳዋ ተከላካዮች ፈተና ሲሆን ታይቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካይ አፈትልኮ በመውጣት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ታትሯል። የግብ ዘቡ ፍሬው አናት በመላክ ያስቆጠራት ጎልንም መጥኖ የላከበት መንገድ ጎል ፊት አይናፋር እንዳልሆነ ያስመሰከረ ነበር።
በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ
በምርጥ ብቃቱ ላይ በመገኘት የውድድር ዓመቱን እያሳለፈ የሚገኘው በረከት ምንም እንኳን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውቶ ድል ማድረግ ባይችልም በጨዋታው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲሰነዝር አይተናል። በረከት ምንም እንኳን ባይሳካለትም ከተሰለፈበት የግራ መስመር እያጠበበ ወደ ሳጥን በመግባትም ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ግብ እየላከ ለቡድኑ የግብ ምንጭ ለመሆን ሲሞክር ነበር። ከዚህ ውጪ ግን የበዛብህ ጎል ሲቆጠር አማኑኤልን ተጭኖ ኳስ እንዲሳሳት በማድረግ ከግብ አስቆጣሪው ጋር አንድ ሁለት ተጫውቶ የመጨረሻ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማን 3-1 መርታት የቻለው አዳማ ከተማ ግብ የማስቆጠር ችግሩን አስተካክሎ በቀረበበት ጨዋታ ሦስት ነጥቦች አሳክቷል። ለዚህ የቡድኑ ድክመት መሻሻል አሰልጣኙ የቅርፅ እና የተጫዋቾች ምርጫ ለውጥ በማድረግ የተጋጣሚን ደካማ ጎን በአግባቡ ተጠቅመው ቡድናቸውን ለድል አብቅተዋል። ከአንድ በላይ ግብ ካስቆጠረ 12 ሳምንታት የሆነው አዳማ የመከላከል ጥንካሬው ሳይጋለጥ የፊት ክፍተቱን በማሻሻሉ በሁለት ግብ ልዩነት ጨዋታውን ፈፅሟል።
ተጠባባቂዎች
ሰዒድ ሀብታሙ
ወርቅይታደስ አበበ
አሸናፊ ፊዳ
አማኑኤል ጎበና
በቃሉ ገነነ
ዱሬሳ ሹቢሳ
አሜ መሐመድ