ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ15ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አመሻሽ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ በዚህ መልኩ ቃኝተነዋል።

የአዳማ እና ሀዋሳ ግንኙነት ለወትሮውም ቢሆን ሜዳ ላይ ጥሩ ፉክክር ከሚደረግባቸው መርሐ ግብር አንዱ ሲሆን ነገ ከድል መልስ መገናኘታቸው ደግሞ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ ያደርገዋል። በድሬዳዋው ውድድር የመጀመሪያ ድሉን ከጥሩ ብቃት ጋር ያሳካው አዳማ ከተማ ነጥቡን 20 ማድረስ ሲችል ነገ አሸንፎ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማው ሲሄድ ራሱን ለዋንጫ ፉክክሩ አስጠግቶ መጀመርን ይፈልጋል። ከባህር ዳሩ ሽንፈት ውጪ በድሬ ቆይታው ሙሉ ነጥቦችን ሲሰበስብ የቆየው ሀዋሳ ከተማም የምስራቋ ከተማ ቆይታውን በድል በመቋጨት እስከ ጊዮርጊስ ጨዋታ አለፍ ሲልም በሊጉ መሪ ውጤት ላይ ተመስርቶ እስከ ሁለተኛው ዙር መጀመር ድረስ በሰንጠረዡ አናት ለመቀመጥ የነገው ድል እጅግ አስፈላጊው ይሆናል።

አዳማ ከተማ ድሬዳዋን በረታበት ጨዋታ በአቀራረቡ ውስጥ ጎሎት የነበረውን ቀመር ያገኘ ይመስላል። ሁለት ግብ ካስቆጠረበት የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ በ90 ደቂቃ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ከብዶት የነበረው ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ይህም የመከላከል ጥንካሬውን የሚመጥን የማጥቃት መልክን ለመላበስ አንድ እርምጃ እንደተራመደ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በድሬው ጨዋታ የቅርፅ ለውጥ በማድረግ 3-5-2ን የተገበረው አዳማ በመስመር ተመላላሾቹ የሜዳ ቁመት እንቅስቃሴ የተመጣጠነ የማጥቃት እና መከላከል ተሳትፎን በማግኘት ከኋላ ያለው ጠንካራ ጎን እንዳይዳከም ማድረግ ሲችል በማጥቃቱ በኩል ደግሞ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በር ተከፍቶለታል። ከዚህ መነሻነትም ከፊት ለተፈጠረው የዳዋ አሜ ጥምረት ቀጥተኛ ጥቃቶች ነገሮች ምቹ ሆነዋል።

የነገው ጥያቄ ታድያ ከኳስ ጋር ብዙ በሚቆየው የድሬዳዋ ጨዋታ ላይ የሰራው ቀመር ቀጥተኝነት በቀላቀለው እና በቅርፅ ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነው ሀዋሳ ጋር የሚተገበርበት መንገድ ይሆናል። ወረቀት ላይ ከአዲሱ ቅርፅ ጋር አብሮ የጎላው ዘካሪያስ ዮሴፍ እና አማኑኤል ጥምረት በመሀል ሜዳው ፍልሚያ ከሀዋሳ የመሀል ክፍል አንፃር የተሻለ ጉልበት ያለው መስሎ ይታያል። ይህ ጥንካሬ በመስመር ተመላላሾቹ ከታገዘ እና ሀዋሳ ተስቦ በሚመጣባቸው አጋጣሚዎች ሁለቱን አጥቂዎች ያማከሉ የተስተካከሉ ኳሶችን ወደፊት ማድረስ ከቻለ ተጋጣሚውን መጉዳት የሚችልበት አግባብ ሊፈጠር ይችላል። ከዚህ ውጪ ለአዳማ አስጊው የሚሆነው ነጥብ የግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ተደጋጋሚ ስህተቶች ናቸው። ከሀዋሳ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጥንካሬ እና ውህደት አንፃር ሲታይ ይህ ድክመት ካልተሻሻለ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካኝ ቡድን ዳግም ዋጋ ለመክፈል መገደዱ የሚቀር አይመስልም።

ሀዋሳ ከተማ በየጨዋታዎች ላይ ከፍ ያለ ፍልሚያ ከተጋጣሚዎቹ ቢመጣም እስከጨዋታው ፍፃሜ በሚያደርገው ተጋድሎ ውጤት ይዞ የመውጣት ባህሪው አሁንም ቀጥሏል። በተጠበቀው መልኩ የእንቅስቃሴ ብልጫ መውሰድ ባልቻለበት የመከላከያው ጨዋታ ውጤት ይዞ የወጣበት መንገድ ሲታይ ደግሞ ‘በድክመት ውስጥም ማሸነፍ’ የሚለውን የዋንጫ ተፎካካሪዎች ባህሪ አላብሶት ታይቷል። ይህ ቡድናዊ ባህሪ ከበድ ያለ ፍልሚያ ለሚስተናገድባቸው ለእንደነገ ዓይነት ጨዋታዎች እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ዕሙን ነው። በእንቅስቃሴም ቢሆን እንደተጋጣሚው ሁኔታ ስትራቴጂው የሚቀያየረው የቡድኑ የፊት መስመር የሦስትዮሽ አስፈሪነቱን ጠብቆ መቀጠሉ ሌላው የሀዋሳ ስብስብ በጎ ጎን ሆኖ ይነሳል።

የአሰልጣኝ ዘርዓይ ቡድን ከሦስቱ አጥቂዎች መሀከል አንዱ የሆነው ኤፍሬም አሻሞን አንዳንዴ ሙሉ ለሙሉ በመስመር አጥቂነት አልያም በተለይም ከኳስ ውጪ ወደ አማካይነት የቀረበ ሚና ሲሰጠው ይስተዋላል። ይህ ታክቲካዊ መላ ከነገው ጨዋታ አንፃር ሲታይ እንደ ዳዊት እና አብዱልባስጥ ዓይነት ንፁህ የተከላካይ አማካዮችን ሳይጠቀም ለሚገባው ቡድን መሀል ላይ የሚጠብቀውን ፍልሚያ አንፃር ኤፍሬምን ወደ መሀል በማስጠጋት ሊተገበር እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ በተለየ ግን እስካሁን የቡድኑ የኋላ መስመር ዋና ደጀን በመሆን ሲያገለግል የቆየው ላውረንስ ላርቴ በቅጣት አለመኖር ሽግሽጎችን አሊያም የቅርፅ ለውጥ ሊያስከትል መቻሉ ለቡድኑ ዋነኛው ክፍተት ሊሆን ይችላል። የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ይህን ክፍተት የሚቀርፉበት የትኛውም መንገድ ግን የሀዋሳን አቀራረብም ሆነ የአዳማን ምላሽ የመወሰን አቅም እንዳለው ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

ሀዋሳ ከተማ ቸርነት አወሽን በጉዳት ሲያጣ ላውረንስ ላርቴ ደግሞ በቅጣት ምክንያት በሜዳ ላይ የማንመለከተው ተጫዋች ነው። አዳማ ከተማ በአንፃሩ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ጨዋታውን ይጀምራል።

ጨዋታው በሊዲያ ታፈሰ የመሀል ዳኝነት ሲመራ ፋሲካ የኋላሸት እና ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት በላይ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን ድረስ በሊጉ 39 ጊዜ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች 87 ግቦች ሲመዘገቡ 46 በሀዋሳ ከተማ 41 ደግሞ በአዳማ ከተማ ስም ተቆጥረዋል። ሀዋሳ 18 አዳማ ደግሞ 10 ጊዜ ድል ሲቀናቸው በቀሩት 11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።

አዳማ ከተማ (3-5-2)

ጀማል ጣሰው

ሚሊዮን ሰለሞን – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ

ጀሚል ያዕቆብ – አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዘካሪያስ ከበደ – ደስታ ዮሐንስ

አሜ መሀመድ – ዳዋ ሆቴሳ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

መሐመድ ሙንታሪ

አዲስዓለም ተስፋዬ – ፀጋሰው ድማሙ – ወንድምአገኝ ማዕረግ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድማገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሀኔ ብርሀኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ