ዐፄዎቹ ከድንቅ ብቃት ጋር ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በአንደኛው ዙር የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን የገጠሙት ፋሲል ከነማዎች ከጨዋታ የበላይነት ጋር ከሰሞኑ የተለየ የማሸነፍ ረሐብ አሳይተው ድሬዳዋ ከተማን 4-0 በመርታት ዙሩን በጥሩ ውጤት አጠናቀዋል።

ፋሲል ከነማ በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገ ሲሆን በዚህም ሚኬል ሳማኬ፣ ከድር ኩሊባሊ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ፍቃዱ ዓለሙን አስወጥተው በምትካቸው ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ኦኪኪ አፎላቢን ተከትተዋል። በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማዎች በአዳማ ከተሸነፈው ስብስብ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ፍሬው ጌታሁን ፣ ዐወት ገ/ሚካኤል ፣ ሙኸዲን ሙሳ ፣ አብዱረህማን ሙባረክ ፣ ማማዱ ሲዲቤን አስወጥተው በምትካቸው ደረጀ ዓለሙ ፣ አወዱ ናፊዩ ፣ እንየው ካሣሁን ፣ ሄኖክ አየለ እና ሳሙኤል ዘሪሁንን በመተካት ቀርበዋል።

በጨዋታው የተጫዋቾች አደራደር ለውጥ በማድረግ በኃላ ሦስት ተከላካዮች የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ጥሩ አጀማመርን ማድረግ ችለዋል ፤ በተለይም በ4ኛው ደቂቃ ሄኖክ አየለ አመቻችቶ በፋሲል የመሀል ተከላካዮች መካከል ባቀበለው ኳስ ከፋሲሉ ግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ወጣቱ ሳሙኤል ሳይጠቀምባት የቀረችው አጋጣሚ በጣም አስቆጭ ነበረች።

ነገርግን በሂደት ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ በደንብ ራሳቸውን ወደ ጨዋታው ማስገባት የቻሉት ፋሲል ከነማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በቁጥር በርከት ካለው ነገር ግን ካልተደራጀው የድሬዳዋ ተከላካይ መስመር በስተጀርባ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል ፤ በ18ኛው ደቂቃም ሽመክት ጉግሳ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ በሞከሩት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል።

በ20ኛው ደቂቃ ግን ፋሲል ከነማዎች መሪ መሆን ችለዋል ፤ በግሩም የቅብብል ሂደት ወደ ድሬዳዋ ሳጥን መድረስ የቻሉትን ኳስ በረከት ደስታ በግሩም ሁኔታ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ በደረጀ ዓለሙ ስህተት ታግዞ እንቅስቃሴውን ያስጀመረው ሽመክት ጉግሳ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ፋሲሎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ቀርበው ነበር በ24ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ከተከላካይ ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ሳጥኑ ያሳለፈውን ኳስ በረከት አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራውን ጀረጀ ዓለሙ ሊያድንበት ችሏል።

በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ከቆመ ኳስ መነሻ ሳሙኤል ዘሪሁን በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ሙከራ የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ሙከራ ነበረች።

በመጀመሪያው አጋማሽ መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች አደገኛ የነበሩት ፋሲሎች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ማጥቃታቸው ላይ በተወሰነ መልኩ ከመስመር እንዲሁም በረጃጅም ኳሶችን ጨምረው ብቅ ብለዋል።

በ56ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከራሱ ሜዳ በረጅም የላከውን ኳስ አውዱ ናፊዮ በአግባቡ መከላከል አለመቻሉን ተከትሎ አኪኪ አፎላቢ ዳግም በደረጀ ዓለሙ ስህተት ታግዞ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በደቂቃዎች ልዮነት ፋሲሎች በግሩም ሂደት ወደ ድሬዳዋ ሳጥን ከደረሱ በኃላ ሽመክት ጉግሳ ከሳጥኑ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ በመምታት የቡድኑን መሪነት ወደ መሪነት ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

በጨዋታው እድሎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ የተዋጣላቸው የነበሩት ፋሲሎች አሁን ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለው ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል ፤ 73ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደምሴ ከአውዱ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ የተነጠቀውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ አግኝቶ ያቀበለውን ኳስ በረከት ደስታ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ግሩም ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በአጋማሹ ይበልጥ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ወደ ቀደመ አደራደራቸው መመላሳቸውን ተከትሎ ጥሩ ቢመስሉም በጥቅሉ ግን ደካማ ነው በዚህም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ፍፁም ተቸገረው ተስተውሏል ፤ አብዱረህማን ሙባረክ እና መኸዲን ሙሳ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ ተጠቃሽ ነገር በጨዋታው ሳያደርጉ ጨዋታውን ፈፅመዋል።

ጨዋታው በፋሲል ከነማዎች የ4-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲሎች በ26 ነጥብ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ድሬዎች ደግሞ በ16 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።