የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የሚያደርገውን ዝግጅት ቀጥሏል፡፡ ቡድኑን እደአዲስ የተቀላቀለው አብዱልከሪም መሃመድ እና ትላንት አዲስ አበባ የገበው ሽመልስ በቀለም ልምምዳቸውን ዛሬ ጀምረዋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በዛሬው ልምምድ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ላይ ልምምድ ሲያሰሩ የተስተዋለ ሲሆን አጥቂው ሙሉአለም ጥላሁን ዛሬም ልምምድ መስራት አልቻለም፡፡ የመከላከያው አጥቂ ብሄራዊ ቡድኑ ያደረጋቸውን ልምምዶች እስካሁን ያልሰራ ሲሆን ከዚህ በኋላ ከጉዳቱ አገግሞ ሰኞ ወደ አልጄርያ በሚጓዘው ስብስብ ውስጥ የመካተቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን በዛሬው ልምምድ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የህክምና እርዳታ በማግኘት ወደ ልምምዱ ተመልሷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጉዳት እና በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ዘዴዘርት ዋርየርስን ለመግጠም ሰኞ ምሽት ወደ አልጄርያ ቢልዳ ከተማ ያቀናል፡፡ ታፈሰ ተስፋዬ ፣ ስዩም ተስፋዬ እና ሙሉአለም ጥላሁንን (ሙሉአለም ከቡድኑ ውጪ መሆኑ አልተረጋገጠም) በጉዳት ፣ ሳላዲን ሰኢድን ደግሞ ለጨዋታ ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት ያጣው ብሄራዊ ቡድናችን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ሌላ እክል ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቲፒ ማዜምቤ ጋር እሁድ ከቀትር በኋላ የመልስ ጨዋታውን አድርጎ ሰኞ ምሽት አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ ደግሞ በዛው ቀን ምሽት 04፡00 ላይ ወደ አልጄርያ ይጓዛል፡፡ በዚህም ምክንያት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅት ያላደረጉት ራምኬል ፣ በሃይሉ ፣ አስቻለው እና አሉላ ከኮንጎ መልስ ሁለት ሰአት ብቻ እረፍት አድርገው ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ጉዞ ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡