​የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 4-0 ድሬዳዋ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ በመቀመጫ ከተማው እየተጫወተ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ያለፉት ጨዋታዎች ጠፍቶ የነበረው የቡድኑ ረሀብ ዛሬ ጎልቶ ስለመውጣቱ?

መጀመሪያ እዚህ ተጫውተን በጊዮርጊስ 4ለ0 የተሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ በዐምሮ ደረጃ ብዙ ነገር ነበረው። ከዛ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ነው ያደረግነው። ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያቶች በጨዋታ እድገት እያሳየን ብንመጣም አጨራተስ ላይ የነበሩን ነገሮች ጥሩ አልነበሩም። ድሬዳዋ ላይ ከ100% ስኬታማ የነበርነው 44% ነው። ይሄ ጥሩ አይደለም። ራሳችን ላይ የነበሩ አንዳንድ ጥቃቅን ጉድለቶችን አርመን ዛሬ ባሸነፍንበት ስነ-ልቦና ለሁለተኛ ዙር ዝግጅት ስለምንሄድ ጥሩ ነው።

ፊት መስመር ላይ የነበረው የቡድኑ አፈፃፀም?

ጥሩ ነው። 9 ሰዓት ያለው ፀሀይ ከባድ ነው። እንደ ማታ አይደለም። ይህም ሆኖ ቅንጅቱ የተሻለ ለውጥ አለው። ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።

ድሬዳዋ ጨዋታውን የቀረበበትን መንገድ ስላመከኑበት ሂደት?

ድሬዳዋ ለራሱ ነጥብ ለማግኘት እና ለደጋፊው ሲል ይሄንን ማረግ ይጠበቅበታል። አማካይ ላይ ኳስ ይዘን ለመጫወት እና ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የመግባት ብቃታችን ሰፊ ስለሆነ ይሄንን ነገር ለመገደብ አማካይ ላይ 5 ተጫዋች አቁመዋል። ግን ያን ያህል ተጠቅመውበታል ብዬ መናገር አልችልም። ዞሮ ዞሮ የአደራደር ለውጥ ቢኖርም አጠቃቀም ላይ የጎላ ነገር አላየሁም። የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ይታዩ ነበር። ከዛ ግን እየለቀቁልን ነው የሄዱት። በአጠቃላይ ግን የዛሬው ውሏችን በጣም አሪፍ ነበር። 

በሰፊ ግብ ልዩነት ስለማሸነፋቸው?

ብዙ ጎል ለማግባት የኳስ አጠቃቀም፣ የቦታ አያያዝ፣ ከተቃራኒ ተሽሎ መገኘት እና ክፍት ቦታዎችን መጠቀም እንዲሁም የግብ አጋጣሚዎች የምትፈጥርበት መንገድ ያስፈልጋሉ። እነዚህ ከሌሉ ጎል ዝም ብሎ አይመጣም። በዛ ልክ ደግሞ የእነሱም የመከላከል ጥንካሬ እየወረደ መጥቷል። አንደኛ ማጥቃት ይፈልጋሉ መከላከልም ይፈልጋሉ። በዚህ መሐከል ስለነበሩ እኛ ያገኘናቸውን ዕድሎች ተጠቅመናል ብዬ አስባለው።

ፉዐድ የሱፍ – ድሬዳዋ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ)

በጨዋታው ስላደረጓቸው ለውጦች?

መጀመሪያ ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው። ጠንካራ እንደመሆኑ ከኋላ 5 አድርገን በ3 አማካይ እና በ2 አጥቂ ነበር ስንጫወት የነበረው። ከእረፍት በኋላ ግን ይሄንን ለውጥ አድርገን በ4-2-3-1 ለመጫወት ሞክረናል። የሄደው ኳስ እኛ ላይ ይገባል። በጣም የሚገርመው ነገር እኛ እዚህ ጋር እናባክናለን። የሄደው ኳስ ሁሉ እየገቡብን ነበር። የተከላካዮቻችንን የንቃት ማነስ ነው እያየው ያለሁት። አጥቂዎቹም እንደፈለጉ እንዲፈነጩ ነው ያደረጉት። መጀመሪያ መያዝ ሲገናቸው ኳስ ከያዘ በኋላ አንድን አጥቂ ምንም ማድረግ አትችልም። ይሄ ነው የተፈጠረው። ስለዚህ ተከላካዮቻችን ላይ የበለጠ ነገር እንድንሰራ ነው የሚያሳየው።

በሜዳችሁ ያረጋችኋቸውን ጨዋታዎች እንዴት ትገመግማቸዋለህ?

ጥሩ አይደለም። የሜዳችንን ጥቅም መጠቀም አልቻልንም። ሁለተኛ ነገር ደግሞ ጫናም (የደጋፊም ሊሆን ይችላል) ነበር። ይሄንን ጫና ደግሞ ተጫዋቾቼ መቀበል ላይ ደካማ ናቸው።

ቡድኑ ስለነበረው የመከላከል ብቃት?

የብቃት እና የትኩረት ችግር ይመስለኛል። ጥቃቅን ስህተቶች ናቸው ዋጋ እያስከፈሉን ያሉት። በተለይ ተከላካዩ ላይ የመዘበራረቅ ነገር ነው ያየሁት። እዚህ ላይ አስተካክለን በቀጣይ እንመጣለን።