[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከ70 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር የተጫወቱት ሀዋሳ ከተማዎች ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ጎል ተጋጣሚ ላይ አስቆጥረው ድሬዳዋ ከተማን ያሸነፉት አዳማ ከተማዎች ዮሴፍ ዮሐንስን በታደለ መንገሻ ለውጠው ጨዋታውን ሲጀምሩ ሀዋሳ ከተማዎችም ድራማዊ ክስተቶች በበረከቱበት ፍልሚያ መከላከያን ሲረቱ ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ በቅጣት ምክንያት የሌለው ላውረንስ ላርቴን ብቻ በአብዱልባሲጥ ከማል ተክተው ወደሜዳ ገብተዋል።
ጥሩ ፉክክር ማሳየት የጀመረው ጨዋታ በ4ኛው ደቂቃ እጅግ ስል የግብ ማግባት አጋጣሚ አስተናግዷል። በዚህም መስፍን ታፈሰ በመስመሮች መካከል የተረከበውን ኳስ አማኑኤል ጎበናን በመቀነስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግብ ለማግኘት ቢጥርም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ራሱ መስፍን በ10ኛው ደቂቃ ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ ሰንዝሯል። ከመልስ ውርወራ የተነሳውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ለመጠቀም ጥሮ ጀማል ሲመልስበት ያገኘ ሲሆን በጥብቅ ምት ወደ መረብ ቢመታውም ሚሊዮን ሰለሞን ደርሶ አምክኖበታል። አዳማዎች ከጅምሩ አንስቶ ኳሱን ለመቆጣጠር ቢሞክሩም ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን በክፍት ጨዋታ በቀላሉ መፍጠር አልቻሉም።
ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የቀይ ካርድ ሁነት ተከስቶበታል። በተጠቀሰው ደቂቃም ዳዋ ከተከላካይ ጀርባ የተላከለትን ረጅም ኳስ ለመጠቀም ሲሮጥ ቁመታሙ የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ ሰፊውን ሜዳ ለመከላከል ክልሉን ለቆ ወጥቶ ኳሱን በእጁ በማገዱ በጨዋታው አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ ተወግዷል። የተሰጠውን የቅጣት ምትም ራሱ ዳዋ ወደግብ ልኮት ለጥቂት ወጥቶበታል።
አዳማ የቁጥር ብልጫ ማግኘቱን ተከትሎ ጨዋታውን በሚፈልገው መንገድ መቃኘት ቢችልም አሁንም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል እንደ ልብ መግባት አልቻሉም። በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ወደራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ለመከላከል ሲጥሩ ታይቷል። አጋማሹም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አንድም ሙከራ ሳይደረግበት ተጠናቋል።
የታሰቡ እና አስገዳጅ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ የተጀመረው ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከት ይዟል። በ53፣ 54 እና 55ኛው ደቂቃ ግን አዳማ በዘካሪያስ፣ ሚሊዮን እና አብዲሳ አማካኝነት ተከታታይ ሙከራዎች በደቂቃዎች ልዩነት አድርጎ ተመልሷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም አዳማ በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ቢደርስም ጥራት ያለቸው የግብ ዕድሎችም መፍጠር አልቻለም።
መልሶ ማጥቃትን ብቻ የአዳማ ክልል መድረሻ አድርገው መንቀሳቀሳቸውን የተያያዙት ሀዋሳዎች የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው ሰፊ ሜዳ ለመሸፈን በመገደዳቸው ድካም ታይቶባቸዋል። በ79ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተባረክ ኤፌሞ እስከሞከረው ኳስ ድረስም ጀማልን ለመፈተን አልጣሩም። በቀሪ ደቂቃዎችም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ጨዋታው 0-0 ተደምድሟል።
የአቻ ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ21 ነጥቦች ያለበት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ሲያገባድድ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ለሰዓታት የተነጠቀውን የሁለተኛ ደረጃ በ27 ነጥቦች ተረክቧል።