የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 ሀዋሳ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የምሽቱ የአዳማ እና ሀዋሳ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

የቁጥር አድቫንቴጅን ስላለመጠቀማቸው

“እንግዲህ ያው ተቃራኒ ሁልጊዜ ጎዶሎ ሲሆን አንተ ጋር የቁጥር ብልጫ ያለው ቡድን ትንሽ ትዕግስተኛ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ በእረፍትም የተነጋገርነው ያንን ነው፡፡ የቁጥር ብልጫ ስላለን ሜዳ ላይ ነፃ ሰው እየፈለግን ለመጫወት እና ትዕግስተኛ ሆነን ለማጥቃት ነበር፤ ግን አልተሳካም። ያሰብነው እና የተነጋገርነው ፤ ሜዳ ላይ ግን እያደረግን የነበረው ይለያያል። በጣም ትዕግስት ኖሮን ቢሆን የምንፈልገውን ጎል ማግባት እንችል ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡

ዘጠኝ የአቻ ውጤት ከአስራ አምስት ጨዋታ ስለመመዝገቡ

“ብዙም እሱን አላስበውም። በጣም የሚያስጨንቀኝ ሜዳ ላይ ምንድነው ጠንካራ ጎናችን ምንድነው ድክመታችን የሚሉት ናቸው፡፡ ለማሸነፍ በብዙ ጨዋታ ላይ ብልጫ እየወሰድን ያጣነው ምንድነው የሚለውን ነው ማሰብ የምፈልገው። እዛ ላይ እንግዲህ ለሁለተኛው ዙር ያሉብንን ክፍተቶች ሰርተን በደንብ እንመጣለን። ወደ ድሬዳዋ ከመጣን በኋላ የተሻለ ቡድን ሜዳ ላይ ነበረን። ያንን ግን ወደ ውጤት መቀየር ይጠበቅብናል፡፡

የመጀመሪያው ዙር ግምገማ ምን ይመስላል

“እንግዲህ ዛሬ ነው የጨረስነው። በአንደኛው ዙር ምንድነው ያሰብነው ምን አግኝተናል ምን አጥተናል በትክክል ቡድናችን ደካማ ጎኑ ምን ነበር? ጥንካሬውስ? ምንድነው የሚለውን በደንብ የምናየው ይሆናል፡፡ እንደ ቡድን ጥሩ ቡድን ሜዳ ላይ አለን። ግን ያንን ወደ ውጤት መቀየር እስካልቻልን ድረስ የምንፈልገውን ነገር እናሳካለን ብዬ አላስብም፡፡

በሁለተኛው ዙር ስለሚኖሩ ለውጦች

“እናያለን፤ የት ጋር ነው ክፍተት ያለው፤ የምናገኘው ሰውስ ምን አይነት ነው የሚለውን በደንብ አይተን ውሳኔዎችን እናሳልፋለን፡፡

አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለተገኘው ውጤት

“በጨዋታው ግብ ጠባቂያችን ከወጣ በኋላ እንዳሰብነው መጓዝ አልቻልንም። ምክንያቱም ወደ ፕላን ሁለት ነው የምትሄደው። በአስራ ስምንተኛው ደቂቃ ይመስለኛል ልጁ በቀይ ካርድ መውጣቱ እንደገና አንድ ሰው ከመሀል ቀንሰን ነውና መሀል ላይ እንደፈለግን መጫወት አልቻልንም። ባገኘናቸው ረጃጅም ኳሶች ነው ለመሄድ ያሰብነው። ዞሮ ዞሮ ያው አንድ ነጥብም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ደረጃውን ይዘን እንድንቆይ ስለሚያደርገን። ሁለተኛ አማራጫችን ጎላችንን አስጠብቀን ግን በምናገኘው ኳስ ነበር ለመሄድ ያሰብነው። በውጤት ደረጃ መጥፎ አይደለም ። ግን እንቅስቃሴያችን በአጠቃላይ በካርዱ ተበላሽቶብናል ማለት ይቻላል፡፡

በቀይ ካርዱ የተነሳ አጥቂ ከመቀነስ ይልቅ አማካዩ አብዱልባሲጥ ተቀይሮ መውጣቱ

“አዎ እነሱን አይተህ ከሆነ ረጃጅም ኳሶችን ነው መምታት የሚፈልጉት። ስለዚህ በንክኪ የሚጫወት ወይም የሚመጣ አማካይ የለም። በዚህም የተከላካይ አማካይ ማስቀመጡ ለእኛ ጥቅም የለውም። ረጃጅም ኳስ ስለሚጫወቱ በሦስት ተከላካይ እነርሱን በማቆም በምናገኘውን አጋጣሚ ቶሎ በመሄድ የአጥቂ አማካይ ወደ ተከላካይ አማካይ በመቀየር ነው የተጫወትነው። ከእነርሱ ኳሱን ይዞ የሚመጣ አማካይ የሌለ በመሆኑ ለዛ ነው ቅያሪውን ያደረግነው። በአጠቃላይ ሁለት ነገር አስበን ነው። አንደኛ ባገኘነው አጋጣሚ ጎል ለማስቆጠር ነው አጥቂ ያልቀየርነው። ሁለተኛ ደግሞ ቅድም ባልኩት መሀል ላይ ስላልተጫወቱ ለእኛ የሚከብደን ነገር ስሌለነው አጥቂ ያልቀየርነው።

እንደ ቡድን የመጀመርያ ዙር ግምገማ

አንደኛው ዙር በቡድናችን ብዙ ነገር የነበረበት ነው። ቡድናችን ወጥ ሆኖ በመጣበት ነው ዛሬ እንዲህ ያለ ነገር የተፈጠረው። ከመከላከያም ጋር ነበረው ጨዋታ እንቅስቃሴያችን እንደፈለግነው አልሆነም። ምክንያቱም በረጃጅም ኳሶች አጨዋወት የሚመጡ ቡድኖች ላይ ትንሽ ክፍተቶች ይታዩብናል። እርሱ ላይ ጠንክረን መስራት አለብን ። ከዛ ውጭ ግን ድሬደዋ ላይ ያገኘነው ውጤት እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ያገኘነውን የሁለተኛ ደረጃ ውጤት የዲቻን ውጤት ሳይጨምር እያስጠበቅን ነው የምንሄደው ይህ በጣም ጥሩ ነው። ሁለተኛው ዙር ላይ ብዙ ክፍተታችንን አርመን ጠንክረን እንመጣለን አንደኛው ዙር በተለይ ድሬደዋ ላይ ወጥ አቋም ያሳየንበት ነው። ሀዋሳ ላይ ወጣ ገባ ያልንበት ነው። ድሬደዋ ላይ ግን ጠንካራውን ሀዋሳ ማሳየት ችለናል።

ያጋሩ