​ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ነገ 10 ሰዓት በአርባምንጭ እና ሰበታ ከተማ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ እንዲህ ተዳሷል።

ከአዳማ ከተማ በመቀጠል በሊጉ ከፍተኛ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ለተጋጣሚ እጅ አልሰጠም። በተለይ እየተነቃቃ የነበረው ሲዳማን፣ በመቀመጫ ከተማው የሚጫወተው ድሬዳዋን፣ አቡበከር ናስርን የያዘው ቡናን እንዲሁም የሊጉን መሪ ጊዮርጊስን በተከታታይ ባለው ውስን ስብስብ ገጥሞ አለመሸነፉ የሚያስደንቀው ሲሆን ነገም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሰበታን በመርታት ነጥቡን 20’ዎቹ ውስጥ ለመክተት እንደሚጥር ይታመናል። 

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅርቃር ውስጥ እየዳከረ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በበኩሉ እጅግ መጥፎ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን በዓመቱ ያገኘው ብቸኛ ድልም ካለፈ ስድስት ሳምንታት ተቆጥረዋል። ያለፈው የጨዋታ ሳምንት ከመጀመሩ በፊት የቀድሞ ምክትል አሠልጣኙ ብርሃን ደበሌን በመንበሩ ያመጣው ቡድኑም ነገ አርባምንጭን በመርታት በጊዜያዊነት ከውራው ቦታ ለመላቀቅ ተግቶ እንደሚጫወት ይገመታል።

በሊጉ ከአንድ ግብ በላይ በጨዋታ አስተናግዶ የማያውቀው የአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስብስብ ጨዋታዎችን ሲቀርብ ዋነኛ የዕቅድ መሠረቱ ግቡን አለማስደፈር እንደሆነ ይታያል። በድርብ የአራት ተጫዋቾች መስመር (Double block of four) ተጋጣሚ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያሻውን እንዳያደርግ ምቾት የማይሰጥ ሲሆን በተቃራኒው ፈጣን ሽግግር በማድረግ እግሩ የገባውን ኳስ ወደላይኛው ሜዳ በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይታትራል። በተለይ ደግሞ በአብዛኛው መስመሩን ታከው እንዲጫወቱ ሀላፊነት የሚሰጣቸው የመስመር አማካዮቹ ፍጥነታቸውን እንደ ግብ ምንጭነት እየተጠቀመ ከመስመር ለሁለቱ የሳጥን ውስጥ አጥቂዎች ተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶች እንዲደርስ ሲያደርግ ይስተዋላል። ባሳለፍነው ሳምንት ከጊዮርጊስ ጋር ሲጫወትም ይሁ ነገር ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም በአንፃራዊነት ነገ የሚፋለመው ቡድን ደከም ያለ ስለሆነ በጨዋታው የበላይ ለመሆን በድፍረት ኳሱን እንደሚቆጣጠር እና ከራሱ ሜዳ ትንሽ ገፋ አርጎ እንደሚጫወት ይታመናል።

በተቃራኒው ሰበታ ከተማ ደግሞ የሊጉ ብዙ ግብ ያስተናገደ ቀዳሚው ክለብ ነው። ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎችም በተናጥል ቢያንስ አንድ ጊዜ (ትልቁ 5 የገባበት ጨዋታ ነው) መረቡን አስደፍሯል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ ዋና አሠልጣኙ ዘላለምን በጊዜያዊነት አግዶ (በይፋ ባይገለፅም) በቀድሞ ምክትል አሠልጣኙ ብርሃን እየተመራ ከባህር ዳር ጋር ባደረገው ጨዋታ ተሻሽሎ ቀርቧል። የተጋጣሚ ቡድን አሠልጣኝ አብርሃም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንዳሉትም ቡድኑ ከወትሮ በተለየ ቅርፁን በጠበቀ ሁኔታ በጥሩ ተነሳሽነት ሲጫወት ነበር። በቡድናዊ መዋቅርም ለተጋጣሚ ተጫዋቾች ቦታን መንፈግ፣ ወሳኝ ተጫዋችን መቆጣጠር እንዲሁም በፈጣን እና ትንሽ ቅብብል ተጋጣሚ ሜዳ ሲደርስ ታይቷል። ይህ አጨዋወት በተወሰነ መልኩ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዞ ቢታይም በወረቀት የዋንጫ ተፎላካሪ ተደርጎ የሚወሰደውን ባህር ዳር ከአንድ ነጥብ በላይ እንዳያገኝ ማድረጉ ጥልቅ ነገር ነው። ምናልባት በነገው ጨዋታም የተነሳሽነት ስሜቱ አድጎ ወይም ቀጥሎ ከመጣ አርባምንጭ መቸገሩ የማይቀር ነው። በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን እንደ ባለፈው ከኳስ ውጪ ዘለግ ያለውን ጊዜ ለማሳለፍ ሊጥሩ ይችላሉ። በዋናነት ደግሞ ባለፉት ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ዱሬሳ በሚሰለፍበት መስመር የሚያገኟቸውን ኳሶች ቶሎ ቶሎ ሊልኩ ይችላሉ።

የግብ ማግባት ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ የመፍጠት አልፎም የተገኙትን የመጠቀም ችግር ያለባቸው ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ከወትሮው በተለየ ስል መሆን ይገባቸዋል። ከላይ በገለፅነው መንገድ አርባምንጭ አጠቃላይ የቡድኑ መሠረት በመከላከል ላይ መመስረቱ እንዲሁም ሰበታ ከወትሮ በተለየ ባለፈው ሳምንት ጥብቅ ባህሪ ማሳየቱ በሁለቱም በኩል በቀላሉ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ሊስተናገዱ እንደማይችሉ ይጠቁማል። ምባልባትም የቆሙ ኳሶች ጨዋታውን ሊወስኑም እንደሚችል ቀድሞ መገመት ይቻላል።

አርባምንጮች በነገው ጨዋታ ከአንድነት አዳነ ውጪ የሚያጡት ተጫዋች አለመኖሩ ሲገለፅ በባህር ዳሩ ጨዋታ የጭንቅላት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ሙና በቀለም በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ሰበታ ከተማ ደግሞ ነገም የአክሊሉ ዋለልኝ እና ዘላለም ኢሳያስን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አምስት ቢጫ ያየው በረከት ሳሙኤልን ደግሞ በቅጣት አያገኝም።

ይህንን ጨዋታ አባይነህ ሙላት በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ደረጀ አመራ እና ዳዊት ገብሬ ረዳት ደግሞ ዮናስ ማርቀስ ዳኛ ሆነው ጨዋታውን ይከውናሉ።


እርስ በእርስ ግንኙነት

– አርባምንጭ ከተማ እና ሰበታ ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ተገናኝተው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።


ግምታዊ አሰላለፍ 


አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – ኡቸና ማርቲን – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሻሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሀቢብ ከማል

ኤሪክ ካፓይቶ – በላይ ገዛኸኝ


ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ሰለሞን ደምሴ

ጌቱ ኃይለማርያም – ወልደአማኑኤል ጌቱ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – በኃይሉ ግርማ – አንተነህ ናደው

ዱሬሳ ሹቢሳ – ዴሪክ ኒስባምቢ – ሳሙኤል ሳሊሶ