[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ሀ ውድድር ዛሬ በአሰላ ሲጀመር የምድብ ለ ቀሪ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎችም በጎንደር ተካሂደዋል።
ምድብ ሀ
በጎንደር ትናንት የተጀመረው ውድድር ዛሬም በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል። የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አማኑኤል ፈረደም በክብር እንግድነት ተገኝተው ወድድሩን ታድመዋል።
8፡00 ላይ ባህር ዳር ከተማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ተመጣጣኝ እና ማራኪ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢታይም የጠራ የጎል ዕድል እምብዛም አልተመለከትንም። ያም ሆኖ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 25ኛ ደቂቃ ላይ ናትናኤል አብርሃ ከማዕዘን ምት የተገኘ ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ባስቆጠረው ጎል የመጀመሪያውን አጋማሽ እየመሩ ወጥተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የሚያስቆጭ ሙከራ ባይኖርም ተሻሽለው የመጡት ባህር ዳር ከተማዎች ግብ ለማግኘት ደቂቃ አልፈጀባቸውም። 46ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ የኔው የማታ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂ ጨርፎ ያወጣበት ኳስ ወደ ማዕዘን ምት ሲቀየር የተሻማውን የማዕዘን ኳስ ራሱ የኔው የማታ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ከመሸነፍ ታድጓል።
በጨዋታው ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች መካከል የባህር ዳር ከተማው የመሃል ተከላካይ አብነት ሞላ ተስፋ የሚሰጥ ተጫዋች እንደሆነ አስተውለናል።
በመቀጠል በተካሄደው የምድቡ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀዲያ ሀሳዕና ወላይታ ድቻን 4-2 ማሸነፍ ችሏል። በዝናባማ የአየር ሁኔታ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች ለተመልካች አዝናኝ የሆነ እንቅስቃሴ ፣ የተመጣጠነ አካላዊ ቁመና እና ብርቱ ፉክክር ያሳዩ ሲሆን ዝናቡ ለጨዋታ አስቸጋሪ ቢሆንም የቆሙ ኳሶች ላይ ያገኟቸው አጋጣሚዎችን በአግባቡ የተጠቀሙት ሆሳዕናዎች አሸንፈው መውጣት ችለዋል።
ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ግብ መድረስ የቻሉት ሀድያዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከበደ ነፃ ሆኖ ያገኘውን የጭንቅላት ኳስ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ መሪ ሊሆኑ ተቃርበው ነበር። በረጃጅም ኳሶች ወደግብ የሚደርሱት ሀድያዎች በ18ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሆነዋል ፤ ከርቀት የተመታውን ኳስ ግብ ጠበቂው ይዞ ሲለቀው ትዕግስቱ ደግፌ ወደግብነት ቀይሮ ነብሮቹን መሪ ሆነዋል። ከ10 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ከቀኝ መስመር የተሻማ ኳስን ተከላካዩ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ማሞ ኃይሌ ወደ ግብ ቀይሮ ሁለት ለዜሮ መምራት ችለዋል። በተደጋጋሚ ወደ ግብ ቢደርሱም ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ድቻዎች በአንፃሩ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀሰን ዘለቀ ወደ ግብነት ቀይሮ 2 ለ 1 እየተመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል ።
ከእረፍት መልስም በተደጋጋሚ ወደግብ የደረሱት ወላይታ ድቻዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ በረከት ማንችሎት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ከ2-0 ተመሪነት ወደ አቻነት ጨዋታውን መቀየር ችለዋል። ሀኖም ይህን ያስጠበቁት ለ4ደቂቃ ብቻ ነው፤ 61ኛው ደቂቃ ላይ ማሞ ኃይሌ ከርቀት የተገኘ የቅጣት ምት በማስቆጠር በድጋሜ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል። ድቻዎች ድጋሜ አቻ የሚሆኑበትን አጋጣሚ ከማዕዘን ምት የተሻማ ኳስ ቅዱስ ቄርቆስ በጭንቅላቱ ገጭቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣው የሚያስቆጭ አጋጣሚ የነበረ ሲሆን በጨዋታው መገባደጃ የቆሙ ኳሶች ላይ ለወላይታ ድቻ ፈተና ሆኖ የዋለው ማሞ ኃይሌ በድጋሜ ከርቀት ግሩም የቅጣት ምት አስቆጥሮ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሀት ትሪክ መስራት ችሏል። ጨዋታውም በሆሳዕና 4 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሀድያ ሆሳዕናው የተከላካይ አማካይ እና የሀት ትሪክ ባለቤት የሆነው ማሞ ኃይሌ የቆሙ ኳሶች ላይ ያለው ችሎታ እጅግ የሚበረታ ሲሆን በዚህ ወድድር ላይ ተስፈ ከሚሰጡ ተጫዋቾች መካከልም አንዱ መሆኑን አስተውለናል ።
ምድብ ለ
አሰላ ላይ የሚደረገው የምድብ ለ ውድድር በዝናብ ምክንያት ሁሉም የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነዋል። ትናንት 8፡00 ሊደረግ የነበረው የወላይታ ቱሳ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ዛሬ 3፡00 የተደረገ ሲሆን ፋሲል 3-2 ማሸነፍ ችሏል። ርሆቦት ማትያስ ወደ እረፍት መውጫው ላይ ስያሜውን ከወላይታ ዞን ወደ ቀድሞው ዝነኛ የአካባቢው ክለብ ወላይታ ቱሳ ለቀየረው ቡድን አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ዣቪየር ሙሉ በ50 እና 57ኛው ደቂቃዎች በተከታታይ አስቆጥሮ ፋሲልን ወደ መሪነት አሸጋግሮታል። በ79ኛው ደቂቃ ዋሲሁን አዴማ ወላይታ ቱሳን አቻ ቢያደርግም ዘካርያስ ሰለሞን በጭማሪው ደቂቃ ዐፄዎቹን ባለ ድል ያደረገ ገል አስቆጥሯል።
ቀጥሎ የተደረገው ከትናንት የተሸጋገረው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነበር። በሀዋሳ 3-2 ሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሀቢብ ዛኪር እና ከድር አሊ ጎሎች ሁለት ጊዜ የመምራት እድሉን ቢያገኙም ሀዋሳዎች በበረከት ካሌብ እና ያሬድ ብሩክ ጎሎች ሁለት ጊዜ አቻ ሆነዋል። በመጨረሻም ዚያድ ከድር በ73ኛው ደቂቃ ሀዋሳን ባለ ድል አድርጓል።
የከሰዓት ጨዋታዎች አስድሞ በወጣላቸው መርሐ ግብር መሰረት ስምንት እና አስር ሰዓት ላይ ተከናውነዋል። በቅድሚያ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን ገጥሞ 1-0 ሲያሸንፍ ይነበብ መዝገቡ የምስራቁን ክለብ የድል ጎል አስቆጥሯል። በዕለቱ የመጨረሻ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ጨዋታ ደግሞ መጨረሻ ሰዓት በዐወት ኪዳኔ አማካኝነት በተቆጠረች ጎል ፈረሰኞቹ 1-0 አሸንፈዋል።