ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የጨዋታ ሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሚደረገው የነገ ምሽቱ ፍልሚያ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በተሰጣቸው ግምት ልክ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ያልቀረቡት ባህር ዳር እና ቡና ዕኩል 19 ነጥቦችን ይዘው ነገ ምሽት ይገናኛሉ። በድሬዳዋ ከተማ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ድል ማስመዝገብ ያልቻሉት ሁለቱ ቡድኖች ከድል ከራቁም በተመሳሳይ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት አልፈዋቸዋል። ከውጤት አንፃር አካሄዳቸው ተመሳሳይነት ኖሮት ሲገናኙ ማናቸው ከ20 በላይ ነጥብ ይዘው ውድድሩን ያጋምሳሉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የነገው ፍልሚያቸው ይጠበቃል።

ባህር ዳር ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ባማከለ የጨዋታ አቀራረብ በመጨረሻ ጨዋታው ሰበታ ከተማን ሲገጥም እምብዛም አመርቂ እንቅስቃሴ አላደረገም። በተሻለ ሁኔታ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ባሳካባቸው ደቂቃዎችም በሚፈልገው መጠን ሰብሮ ሲገባ አይታይም ነበር። በስብስቡ የጨዋታ ባህሪ ውስጥ የመልሶ ማጥቃት ቅንጣትም ያለው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ግን ለኳስ ቁጥጥር ያለው ፍላጎት ከበፊቱ ቀንስ ያለ እንደሚሆን ይገመታል። ይልቁኑም የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሀል ሜዳ አጠግቶ ከፊት ደግሞ የቡናን የኳስ ምስረታ ዑደት ከጅምሩ ጫና ውስጥ ከትቶ ለመጫወት እንደሚያስብ ይገመታል። ለዚህም ይረዳው ዘንድ ፈጣኖቹ አጥቂዎቹን በማጥቃት ሽግግር ወቅት የሚያስመለክቷቸውን አፈትላኪ ሩጫዎች በቡና ሳጥን ዙሪያ ከኳስ ውጪም ሲሆኑ እንዲከውኑ የሚጠብቅ ይመስላል።

ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች በሦስት ተከላካይ ከሚጀምር አደራደር አተገባበሩ የተጫዋች ምርጫው እና ስትራቲጄው ቢለያይም ወደ 4-2-3-1 የመጣው ባህር ዳር የነገ አሰላለፉ የተጋጣሚውን ጥቃት ከማቋረጥ መነሻነት ወይንስ የራሱን የማጥቃት ሂደት ከመጀመር አንፃር ይመሰረታል የሚለው ተጠባቂ ይሆናል። ቡድኑ ካለበት ሁነኛ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተመላላሾች ጊዜያዊ እጥረት አንፃር ሦስት የኋላ ተከላካይ ላይጠቀም እንድሚችል ይታሰብ እንጂ በሰበታው ጨዋታ ዋና ድክመቱ የነበረውን የኮሪደሮች እንቅስቃሴ ማስተካከል ግን ነገ እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። ለዚህም አሰልጣኝ አብርሀም ከጉዳት የተመለሰው መሳይ አገኘሁን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሲገመት በሁለቱ መስመሮች ከኳስ እና ከኳስ ውጪ ከቡና የመስመር አጥቂዎች ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ የቁጥር ብልጫን በየሜዳ ክፍሉ ላይ በመፍጠር ለመወጣት የቦታው ተሰላፊዎች ሚና ወሳኝ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጩ ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ በኋላ ከፋሲል ጋር ጨዋታውን በጥሩ ጉልበት ሲጀምር ታይቷል። ይህንን ንቃት ለሙሉ ዘጠና ደቂቃ ማስቀጠል ባይችልም በነገው ጨዋታ ግን ከኳስ ውጪ ክፍተቶችን ለመንፈግ በሚንቀሳቀሰው ተጋጣሚው ፊት በተገቢው የትኩረት እና የታታሪነት ደረጃ ላይ መገኘት የግድ ይለዋል። ቡድኑ ከኋላ መስርቶ በመውጣት ሂደቱ ላይ በፋሲሉ ጨዋታ ያገኘው የአበበ እና ገዘኸኝ ጥምረት ነገ ይበልጥ ከፍ ያለ ጫና እንደሚገጥመው ሲጠበቅ በቦታው ከነበረበት ድክመት አንፃር ግን የባህር ዳር ከተማ የወገብ በላይ ጫና በመቋቋም ኳስ የማሰራጨት አቅሙ በጨዋታው ሂደት ላይ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ይህን ነጥብ ለቡና ወሳኝ የሚያደርገው ደግሞ ከተጋጣሚው የመጀመሪያ የጫና ወጥመድ አልፎ መሀል ሜዳውን የተሻገረ ክፍተት በማግኘት ኳስ ተቀባይ ተሰላፊዎችን በቅብብል ከማግኘት አንፃር ነው።

አምና በነበረው የፈጠራ እና የግብ ብቃት ላይ የማይገኘው የቡድኑ አማካይ እና የፊት መስመር ስብጥርም እንዲሁ በጣና ሞገዶቹ የሜዳ ክፍል ላይ የሚኖረው የቅብብል ጥራት ወሳኝ ይሆናል። ቡድኑ ከመጀመሪያው ወጥመድ አልፎ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ጋር ከደረሰ በራሱ ሜዳ ላይ ከሚገጥመው በመጠኑ ቀለል ያለ ፍልሚያ ሊጠብቀው ይችላል። ሆኖም አማካዮቹን ወደ ሳጥን በማስጠጋት እንዲሁም የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ተሳትፎ በመጨመር በቦታው የቁጥር ብልጫን ማሳካት ከቻለ ብቻ ወደ ተጋጣሚው ሳጥን መድረስ ይሆንለታል። በዚህ ረገድ ከጉዳት የተመለሰው የሚኪያስ መኮንን የጨዋታ ብቁነት በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት እክል ሊሆንበት ቢችልም ተጨዋቹ ወደ መሀል አጥብቦ የሚገባባቸው ቅፅበቶች ለእነ አቡበከር የማፈትለኪያ ክፍተቶችን ሊተውላቸው እንደሚችል ይታመናል።

ባህር ዳር ከተማ የመስመር ተጫዋቾቹ ግርማ ዲሳሳ እና አህመድ ረሺድን በቅጣት ሲያጣ ጉዳት ላይ የሰነበቱት መሳይ አገኘሁ እና በረከት ጥጋቡ እንዲሁም በቅርቡ ያገገመው ኦሴይ ማዉሊ ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ተሰምቷል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የራጅም ጊዜ ጉዳት ከገጠመው ዊሊያም ሰለሞን ሌላ የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።

ቴዎድሮስ ምትኩ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት እንደሚመራ ሲጠበቅ አበራ አብርደው እና ዘሪሁን ኪዳኔ በረዳትነት እያሱ ፈንቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በእስካሀኑ አራት ግንኙነታቸው ተመጣጣኝ ውጤት ያላቸው ቡና እና ባህር ዳር አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና ዘጠኝ እንዲሁም ባህር ዳር አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – መናፍ ዐወል – ሰለሞን ወዴሳ – ሳለአምላክ ተገኘ

አለልኝ አዘነ – በረከት ጥጋቡ

ዓሊ ሱለይማን – ፍፁም ዓለሙ – አብዱልከሪም ኒኪማ

ኦሴ ማዉሊ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – ገዛኸኝ ደሳለኝ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ሮቤል ተክለሚካኤል

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር – አላዛር ሽመልስ

ያጋሩ